በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል ጋዛ ውስጥ ሁለት የእስላማዊ ጂሃድ ተዋጊ አዛዦች መግደሏን ገለጸች


ከደቡብ እስራኤል እንደታየው በጋዛ ሰርጥ ከሚገኙት ሕንፃዎች ጀርባ ፀሐይ ስትጠልቅ ትታያለች፤ እአአ ሃምሌ 17/2024
ከደቡብ እስራኤል እንደታየው በጋዛ ሰርጥ ከሚገኙት ሕንፃዎች ጀርባ ፀሐይ ስትጠልቅ ትታያለች፤ እአአ ሃምሌ 17/2024

የእስራኤል የጦር ኅይል ዛሬ ሐሙስ ጋዛ ከተማ ውስጥ ባደረሰው የአየር ጥቃት ሁለት ከፍተኛ የእስላማዊ ጂሃድ ቡድን ከፍተኛ አዛዦችን ገድለናል ሲል አስታወቀ፡፡

ከተገደሉት የእስላማዊ ጂሃድ ተዋጊ አዛዦች መካከል አንደኛው እአአ ጥቅምት ሰባት በደቡባዊ እስራኤል በተፈጸመው ጥቃት የተሳተፈ መሆኑን የእስራኤል የመከላከያ ኃይሎች አስታውቋል፡፡

የእስራኤል ኅይሎች ማዕከላዊ ጋዛ ውስጥም የአየር ጥቃት ያደረሱ ሲሆን የምድር ጦሩ ታንከኞች ደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ከተማ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ጥቃት ማድረሳቸው ተገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ደቡባዊ ጋዛ ውስጥ በቀጠለው ውጊያ የተነሳ ስድሳ አልጋዎች ያሉት የቀይ መስቀል ሆስፒታልን ጨምሮ የጤና ተቋማቱን በሙሉ በጽኑ የተጎዱ ቁስለኞችን ለመንከባከብ የማይችሉበት ደረጃ እየደረሱ መሆናቸውን ጥቅሶ አስጠንቅቋል፡፡ የሀማስ ታጣቂዎች እአአ ጥቅምት ሰባት እስራኤል ላይ ባደረሱት ጥቃት 1200 የሚሆኑ ሰዎች ገድለው 250 የሚደርሱ ሰዎች ጠልፈው መውሰዳቸውን ተከትሎ ጦርነቱ ተቀስቅሷል፡፡ 116 ዜጎቿ አሁንም በሃማስ እጅ እንዳሉ እስራኤል ትናገራለች፡፡ የእስራኤል የጦር ሠራዊት እንዳለው አርባ ሁለቱ ታጋቾች ሞተዋል፡፡

የጋዛ የጤና ሚንስቴር እንዳለው እስራኤል ጋዛ ውስጥ በየብስ እና በአየር ባደረሰቻቸው ጥቃቶች ከሠላሳ ስምንት ሺህ ሰባት መቶ በላይ ሰዎች ገድላለች ፡፡

ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮኑ የጋዛ ነዋሪ ውስጥ ሦስት አራተኛ የሚሆነው ከመኖሪያው ተፈናቅሏል፡፡ ጠቅላላ ሕዝቡ መባል በሚችል ደረጃ የረሃብ ቸነፈር አደጋ አፋፍ ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG