በቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ላይ ትላንት ቅዳሜ በተፈጸመው የግድያ ሙከራ ተጠርጣሪው ቶማስ ማቲው ክሩክስ የተባለ የሃያ ዓመት ሰው መሆኑን የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ኤፍ.ቢ.አይ አስታወቀ።
የኅዳሩ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ ተፎካካሪው ትረምፕ "በትለር" በተባለች የፔንሲልቬኒያ ክፍለ ግዛት ከተማ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ የተተኮሰባቸው ጥይት ጆሮአቸው ላይ አቁስሏቸዋል።
እማኞች እንዳሉት አጥቂው በያዘው ጠመንጃ ተኩስ የከፈተው ትረምፕ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ሲያደርጉ በነበረበት ቦታ አቅራቢያ ካለ ህንጻ ጣሪያ ላይ ሲሆን ሕግ አስከባሪዎች በጥይት መትተው ገድለውታል።
በጥቃቱ ቢያንስ አንድ የድጋፍ ስብሰባው ታዳሚ ሲገደል ሌሎች ሁለት ሰዎች በአስጊ ሁኔታ ቆስለዋል።
ተጠርጣሪው ማቲው ክሩክስ የቀድሞው ፕሬዝደንት የምርጫ ዘመቻ ቅስቀሳ ላይ ከነበሩባት ከበትለር ከተማ መኪና የአንድ ሰዓት ርቀት ላይ የምትገኝ "ቤተል ፓርክ" የተባለች ከተማ ነዋሪ እንደነበረ ኤፍ ቢ አይ አስታውቋል።
መግለጫው በጥቃቱ ዙሪያ ምርመራ መቀጠሉን አስታውቆ መረጃ ያለው ሰው በአስቸኳይ ባለሥልጣናትን እንዲያነጋግር ጥሪ አቅርቧል። ስለተጠርጣሪው ግን ሌላ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
የቀድሞው ፕሬዝደንት ጥቃቱን ተከትሎ ለሕክምና ከተወሰዱበት ሆስፒታል ሌሊት ላይ ወጥተዋል። በማኅበራዊ መገናኛቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ በተተኮሰባቸው ጥይት ቀኝ ጆሮአቸው ላይ መቁሰላቸውን ገልጸው ። "ደህና ነኝ" ብለዋል። እንዲህ ያለ ድርጊት በእኛ አገር መድረስ መቻሉን ለማመን ያዳግታል" ሲሉም አክለዋል።
ዛሬ ንጋት ላይ የ የፒትስበርግ ክተማ የፊዲራሉ ምርመራ ቢሮ የመስክ ቢሮ ልዩ መኮንኑ ኬቭን ሮጄክ በሰጡት ቃል " አጥቂው አራት እና አምስት ጥይት እስኪተኩስ ተደርሶበት አለመገደሉ ያስገርማል" ብለዋል። " ጥቃቱን ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው ለጊዜው አናውቅም" ያሉት ባለሥልጣኑ "ያለመታከት ምርመራ ይቀጥላል፥ ምርመራው ወራት ሊወስድ ይችላል" ብለዋል።
ይፋዊ በሆኑ የመራጮች መዝገቦች መሠረት አጥቂው በሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊነት የተመዘገበ ሲሆን በቅርቡ ግን ለአንድ ለዘብተኛ (ሊበራል ) ቡድን የአስራ አምስት ዶላር መዋጮ መስጠቱ በርካታ የዜና ማሰራጫዎች እየተዘገበ ነው።
በቀድሞው ፕሬዝደንት ላይ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ ፊቱንም የተጋጋለ የሆነውን የፕሬዝደንታዊ ምርጫ ፉክክር ይበልጡን ያጋግለዋል፥ አስቀድሞም ውጥረት የተመላባቸው በሆኑት ክርክሮች ላይ ጸብ የሚያጭሩ ንግግሮችን ያባብሳል የሚል ስጋት ተደቅኗል።
በቀድሞው ፕሬዝደንት ላይ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ እና የቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጸም ጥቃትን አጥብቀው በማውገዝ ጠንካራ መግለጫዎች አውጥተዋል።
ከኋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት ትላንት ከመሸ የተሰጠው ቃል ፕሬዝደንት ባይደን ሚስተር ትረምፕን አነጋግረዋቸዋል። የውይይታቸው ይዘት በዝርዝር አልገለጸም። በቤተ መንግሥቱ ቃል መሠረት ፕሬዝደንቱ የቀደመው ዴላዌር በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የመቆየታቸውን የመቆየታቸውን እቅድ ትተው ዛሬ ጠዋት ወደ ኋይት ሐውስ ይመለሳሉ።
ባይደን ጥቃቱን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ "ለርሳቸው፣ ለቤተሰባቸው እና የምረጡኝ ዘመቻ ስብሰባው ላይ ለነበሩት ሁሉ እጸልያለሁ። እንዲህ ያለ ሁከት አሜሪካ ውስጥ ቦታ የለውም። እንደሀገር በአንድነት ልናወግዘው ይገባል" ብለዋል።
የፕሬዝደንት ባይደን የምርጫ ዘመቻም ማንኛውም የውጭ ኮምዩኑኬሽን ለጊዜው እንደሚገታ የቴሊቭዥን ምርጫ ዘመቻ ማስታወቂያዎችንም በአስቸኳይ ለማንሳት እየሠራ መሆኑን አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሪፐብሊካን ፓርቲው ብሐራዊ ኮሚቴ ትላንት በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ ትረምፕ ነገ ሰኞ ሚሉዋኪ ከተማ ላይ በሚከፈተው የፓርቲው ጉባዔ ላይ የመገኘት እቅዳቸውን እንዳልለወጡ አስታውቋል።
የትላንቱን ጥቃት ተከትሎ ለሚስተር ትረምፕ የሚሰጠውን የምስጢራዊ የደህንነት ጥበቃ ደረጃ በሚመለከት ጥያቂዎች ጥያቄዎች እየተነሱ ሲሆን የተወካዮች ምክር ቤት ሪፐብሊካን መሪዎች በጥቃቱ ዙሪያ ሙሉ ምርምራ እንደሚከፍቱ አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም