በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዶናልድ ትረምፕ የግድያ ሙከራ ተጠርጣሪው ቶማስ ማቲው ክሩክስ የተባለ የ20 ዓመት ወጣት መሆኑን ኤፍ ቢ አይ አስታወቀ


በቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ላይ ትላንት ቅዳሜ በተፈጸመው የግድያ ሙከራ ተጠርጣሪው ቶማስ ማቲው ክሩክስ የተባለ የሃያ ዓመት ሰው መሆኑን የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ኤፍ.ቢ.አይ አስታወቀ።

የኅዳሩ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ ተፎካካሪው ትረምፕ "በትለር" በተባለች የፔንሲልቬኒያ ክፍለ ግዛት ከተማ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ የተተኮሰባቸው ጥይት ጆሮአቸው ላይ አቁስሏቸዋል።

እማኞች እንዳሉት አጥቂው በያዘው ጠመንጃ ተኩስ የከፈተው ትረምፕ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ሲያደርጉ በነበረበት ቦታ አቅራቢያ ካለ ህንጻ ጣሪያ ላይ ሲሆን ሕግ አስከባሪዎች በጥይት መትተው ገድለውታል።

በጥቃቱ ቢያንስ አንድ የድጋፍ ስብሰባው ታዳሚ ሲገደል ሌሎች ሁለት ሰዎች በአስጊ ሁኔታ ቆስለዋል።

ተጠርጣሪው ማቲው ክሩክስ የቀድሞው ፕሬዝደንት የምርጫ ዘመቻ ቅስቀሳ ላይ ከነበሩባት ከበትለር ከተማ መኪና የአንድ ሰዓት ርቀት ላይ የምትገኝ "ቤተል ፓርክ" የተባለች ከተማ ነዋሪ እንደነበረ ኤፍ ቢ አይ አስታውቋል።

መግለጫው በጥቃቱ ዙሪያ ምርመራ መቀጠሉን አስታውቆ መረጃ ያለው ሰው በአስቸኳይ ባለሥልጣናትን እንዲያነጋግር ጥሪ አቅርቧል። ስለተጠርጣሪው ግን ሌላ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

XS
SM
MD
LG