ለአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በግል የቀረቡት ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር፣ የባይደን እና ትረምፕ ክርክር በተደረገበት ተመሳሳይ ሰዓት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ላይ መልስ ሲሰጡ አምሽተዋል።
ከአሜሪካዊው ከጋዜጠኛ እና የፖለቲካ አቀንቃኝ ጃን ስታስል ጋራ በ X ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቀጥታ በተላለፈ የአንድ ሰው ክርክር፣ በግል በእጩነት የቀረቡት ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር፣ የራሳቸውን ክርክር “እውነተኛ ክርክር” ሲሉ አሞካሽተው፣ የባይደንን እና የትረምፕን ክርክር ያዘጋጀውን ሲኤንኤን፣ ከሁለቱ ፓርቲዎች ጋራ በመመሳጠር አግልሎኛል ሲሉ ከሰዋል።
“በአሜሪካ የፖለቲካ ስርዓቱ በተጭበረበረ መንገድ በቁጥጥር ሥር የዋለ ነው” ያሉት ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር፣ የእርሳቸው መድረክ ለዲሞክራሲ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
“የመንግስት እና የኩባንያዎች የተቀናጀ ኃይል” ብለው የገለጹትን ለመቃወም ወደ ምርጫው እንደገቡም በመክፈቻ ንግግራቸው አስታውቀዋል።
ሲኤንኤን በክርክሩ ለመቅረብ ያወጣውን መመዘኛም አጥላልተዋል።
ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር፣ 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የወንድም ልጅ ናቸው።
መድረክ / ፎረም