በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩኤስ ምርጫ 2024 የመጀመሪያ ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ጉዳዮች


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የቀድሞው ፕሬዚዳንት እና የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ፣ የ2024 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያ ክርክራቸውን አትላንታ በሚገኘው የሲኤንኤን ቴሌቭዥን ጣቢያ ሲያካሂዱ እአአ ሰኔ 6/2024
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የቀድሞው ፕሬዚዳንት እና የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ፣ የ2024 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያ ክርክራቸውን አትላንታ በሚገኘው የሲኤንኤን ቴሌቭዥን ጣቢያ ሲያካሂዱ እአአ ሰኔ 6/2024

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የቀድሞው ፕሬዚዳንት እና የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ፣ የ2024 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያ ክርክራቸውን አትላንታ በሚገኘው የሲኤንኤን ቴሌቭዥን ጣቢያ አካሂደዋል።

ሁለቱ ተከራካሪዎች ክርክራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ሲጨባበጡ አልታዩም። ለተከራካሪዎቹ የቀረበላቸው ቀዳሚ ጥያቄ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው።ትራምፕ ክርክራቸውን የጀመሩት፣ የአሜሪካ መራጮች ዋና የሚያሳስባቸው ጉዳይ ኢኮኖሚ መኾኑን በመግልጽ ነው።

በሌላ በኩል ፕሬዚዳት ባይደን ሥልጣን ከተረከቡ ወዲህ የዋጋ ግሽበት ቢቀንስም የሸቀጦች ዋጋ አኹንም ከፍተኛ ኾኖ መቀጠሉን ጠቁመው፣ በትራምፕ አስተዳደር ከነበረው የባሰ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ለሚያስቡ አሜሪካውያን ምላሽ የሰጡት ባይደን፣ ውድቀት ውስጥ የገባ ኢኮኖሚ ከትራምፕ መረከባቸውን ተናግረዋል።

የሥራ አጥነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር እና የእርሳቸው አስተዳደር 15 ሺህ አዳዲስ ሥራዎች መፍጠሩን ያመለከቱት ባይደን "አሁንም ተጨማሪ ሥራ ይቀረናል። ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው ሠራተኞች አሁንም ችግር ውስጥ ናቸው" ብለዋል።

በተጨማሪም የመድኃኒት ዋጋ እንዲወርድ ማድረጋቸውን ገልጸው እንደምሳሌ 400 ዶላር ይሸጥ የነበረው የኢንሱሊን ዋጋ ወደ 15 ዶላር መወረዱን አመልክተዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ

"በሀገራችን ታሪክ ታላቅ ኢኮኖሚ ነበረን" ያሉት ትራምፕ በበኩላቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተነሳበት ወቅት የኢኮኖሚ ውድቀት እንዳይከሰት ተገቢውን ወጪ ማውጣታችውን አመልክተዋል። በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ጦርነት አለመኖሩንም ገልጸዋል። "አሜሪካንን አሁን እየጎዳ ነው" ላሉት የዋጋ ግሽበትም የባይደንን አስተዳደር ተጠያቂ አድርገዋል።

ትራምፕ፣ “ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ያቀረቡት ሐሳብ የሀገር ውስጥ ዋጋ ጭማሪ እንዲባባስ አያደርግም ወይ?” ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ፣ እቅዳቸው "እንደ ቻይና ያሉ ሲያከስሩን የነበሩ ሀገራትን ዋጋ ያስከፍላል" በማለት ተከላክለዋል። ትራምፕ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከፍተኛ ገቢ ላላቸው እና ለኮርፖሬሽን ያደረጉትን የግብር ቅነሳ በተመለከተም ፣ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር እንደረዳ ሲያስረዱ ባይደን በበኩላቸው ግብር ቅነሳው ሀብታሞችን ለመርዳት የተደረገ ነው ሲሉ ተችተዋል።

የጽንስ ማቋረጥ መብትን በተመለከተ፣ ጽንስን ለማቋረጥ የሚወሰዱ መድኃኒቶችን ያግዱ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ፣ "አላግድም" ሲሉ ምላሽ የሰጡ ሲኾን አስገድዶ መደፈር፣ የስጋ ዝምድና ባላቸው ሰዎች መካከል እርግዝና ሲፈጠር እና የእናት ሕይወት አደጋ ላይ ሲወድቅ ጽንስ መቋረጥን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

ጽንስ የማቋረጥ መብት ላይ የመወሰኑ ሥልጣን ለግዛቶች መሰጠቱ ትክክል ነው ሲሉ የተከራከሩት ትራምፕ ዲሞክራቶች "የስምንት እና የዘጠኝ ወር" ዕድሜ ያለው እርግዝናን በማቋረጥ "ህይወት ያጠፋሉ" ሲሉም ከሰዋቸዋል።

ባይደን በበኩላቸው ጽንስ ማቋረጥ ሕግ መንግሥታዊ መብት በጠቅላይ ፍርድቤት መሻሩ እጅግ በጣም መጥፎ ውሳኔ መሆኑን በመግለፅ ውሳኔው በእናት እና በሐኪሟ መካከል መሆን እንዳለበት ገልጸው ተሟግተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

በባይደን አስተዳደር በርካታ ሕገወጥ ስደተኞች የአሜሪካንን ድንበር ጥሰው ሀገር ውስጥ መግባታቸውን በተመለከተ ባይደን ለቀረበላቸው ጥያቄ የድንበር ጥበቃ አባላት ቁጥር እና የጥገኝነት ጥያቄዎችን የሚመለከቱ ሰዎችን ቁጥር መጨምራቸውን በመግለፅ ሕገወጥ ስደትን ለማስቆም እንደሚጥሩ ገልጸዋል። ትራምፕ በበኩላቸው "ባይደን ድንበሩን ክፍት አድርገዋል" በማለት ሕገወጥ ስደተኞች እየፈፀሙ ነው ያሏቸውን ወንጀሎች ዘርዝረዋል።

በመጪው ኅዳር ለሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ የሚወዳደሩት ሁለቱ ተፎካካሪዎች የተከራከሩበት ሌላው ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነው።

ፑቲን ጦርነቱን የሚያቆሙት አሁን የያዟቸው የዩክሬን ይዞታዎች በሩሲያ ስር የሚጠቃለሉ ከኾነ እና ዩክሬን የኔቶ አባል የመሆን ጥያቄዋን ካነሳች ብቻ ነው ማለታቸውን ትራምፕ ይቀበሉት እንደሆነ ሲጠየቁ "እውነተኛ፣ ፑቲን የሚያከብረው ፕሬዚዳንት ቢኖረን ኖሮ ዩክሬንን መቼም አይወርም ነበር።" ያሉ ሲኾን "እንደውም ዩክሬንን እንዲወር ያበረታቱት ባይደን ናቸው" በማለት ከሰዋቸዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍጋኒስታን የወጣችበት ሁኔታም ለፑቲን ወረራ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልጸዋል። ባይደን በበኩላቸው ፑቲን የጦር ወንጀለኛ መሆናቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መግደላቸውን እና የሶቪየት ኅብረትን እንደገና ማቋቋም እንደሚፈልጉ በመግለፅ ለዩክሬን የሚሰጠው የጦር መሳሪያ አሜሪካን እያጠነከረ ነው ብለዋል።

የመጀመሪያውን ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ከሚመሩት አንዱ፣ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ጄክ ታፐር፣ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ጥር 6 ቀን 2021 ዓ.ም. የትራምፕ ደጋፊዎች ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ለመቀልበስ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን በማስታወስ፣ “የአሜሪካን ዲሞክራሲ እና ሕገ መንግሥት ለመጠበቅ የገቡትን ቃል ጥሰዋል” ለሚሉ አሜሪካውያን ምላሽ እንዲሰጡ ላቀረበው ጥያቄ፣ ትራምፕ በሰጡት ምላሽ "እስከ ጥር 6 ድረስ የተከበርን ነበር።

እርሱ መጣ እና አሁን ሁሉም ይስቅብናል" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። አክለውም፣ ወደ ምክር ቤቱ እየጎረፈ የነበረውን ሰው በማስተዋል ሊፈጠር ለሚችለው ነገር በመስጋት 10 ሺህ ወታደሮችን ለመመደብ ቢጠይቁም፣ በወቅቱ የምክርቤቱ አፈጉባኤ የነበሩት ናንሲ ፔሎስ እንዳልተቀበሏቸው በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል። ባይደን በበኩላቸው ምክርቤቱ ላይ ጥቃት የፈፀሙትን ሰዎች ያበረታቷቸው ትራምፕ መሆናቸውን እና ምክትል ፕሬዚዳንታቸው ሁኔታውን እንዲያስቆሙ ለሦስት ሰዓታት ቢለምኗቸውም "የሀገር ፍቅር ነው" በማለት ችላ ማለታቸውን ገልጸዋል።

ጥቁር አሜሪካውያንን በተመለከተ በባይደን አስተዳደር ጥቁር አሜሪካውያን ቀድሞ ከነበሩበት የባሰ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ቁጥሮችን በመግለፅ ከሲኤን ኤን ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ባይደን፣ ሲመልሱ የጥቁር አሜሪካውያንን ህይወት ለማሻሻል ብዙ ለውጦችን ማካሄዳቸውን እና የጥቁር አሜሪካውያን ሥራ አጥ ቁጥር እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ጥቁር አሜሪካውያን በአስተዳደራቸው ቅር በመሰኘቱ "አልወቅሳቸውም" ያሉት ባይደን የዋጋ ግሽበቱን ተጠያቂ አድርገዋል።

"የዋጋ ግሽበቱን የፈጠሩት" ባይደን ናቸው ሲሉ ወቀሳ ያሰሙት ትራምፕ በበኩላቸው፣ "ሥልጣኑን ሳስረክባቸው የዋጋ ግሽበት አልነበረም። እርሳቸው ናቸው ያበላሹት" የሚል ምላሽ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት በተመለከተ፤ ባይደን፣ አስተዳደራቸው ያቀረበው የመፍትሄ ሐሳብ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ተቀባይነት ማግኘቱን እና በሦስት ደረጃ ጦርነቱን ማስቆም እንደሚቻል ተናግረዋል። ትራምፕ በበኩላቸው ባይደን "ፍልስጤማዊ ኾነዋል፣ ነገር ግን እነሱም አይወዷቸውም ምክንያቱም መጥፎ ፍልስጤማዊ ናቸው" ብለዋል።

"እስራኤል በሐማስ መቼም ጥቃት አይደርስባትም ነበር" ያሉት ትራምፕ እሳቸው በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት "ኢራን ገንዘብ አልነበራትም። ማንም ከኢራን ጋራ ንግድ እንዲሠራ አልፈቅድም ነበር" ሲሉ ምክንያታቸውን አስረድተዋል።

ፍልስጤም ነፃ ሀገር መሆኗን ይደግፉ እንደሆነ ለተጠየቁት ጥያቄ ትራምፕ "ወደፊት የማየው ይሆናል" ሲሉ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG