በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኤርትራ መሠረታዊ መብቶች ስልታዊ በሆነ መንገድ ታፍነዋል - ተመድ


የኤርትራ ካርታ
የኤርትራ ካርታ

የኤርትራ መንግሥት የሕዝቡን መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች በኃይል እና በዛቻ በማፈን ሥልጣኑን ለማጠናከር እየተጠቀመበት ነው ሲሉ የሰብአዊ መብቶች ባለሞያ አስታወቁ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርት አቅራቢ የሆኑት ሞሐመድ አብደልሰላም ባቢከር ሐሙስ ዕለት ለድርጅቱ ሰብአዊ መብቶች ምክርቤት ባደረጉት ንግግር "በኤርትራ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው። በዘፈቀደ እና በድብቅ የሚፈጸሙ እስር እና የግዳጅ መሰወርን ጨምሮ ከባድ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ያለማቋረጥ ቀጥለዋል" ብለዋል።

ባቢከር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ዓ.ም. ልዩ ዘጋቢ ሆነው በምክርቤቱ ከተሾሙ ወዲህ ለአራተኛ ጊዜ ባቀረቡት በዚህ ሪፖርት "ባለሥልጣናቱ ከግዳጅ የጉልበት ሥራ ጋራ የሚመሳሰል እና ከማሰቃየት እና ኢ-ሰብአዊ ወይም አዋራጅ አያያዝ ጋራ የተቆራኘ፣ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ወታደራዊ ብሔራዊ አገልግሎት ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ቀጥለዋል" ብለዋል።

በሚያሳዝን ሁኔታ ባለፉት ዓመታት ኤርትራ ውስጥ ምንም ነገር እንዳልተለወጠ ማስተዋላቸውን የገለጹት ባቢከር ተመሳሳይ አሳሳቢ ጉዳዮች በተለያየ ጊዜ እንደሚነሱ እና በሀገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ቀውስ የሚያባብሱ ፖሊሲዎችን እና አሠራሮችን ለማሻሻልም ሆነ ለመለወጥ ግን ምንም እርምጃ አለመወሰዱን አፅንዖት ሰጥተው አስረድተዋል።

ባቢከር ለምክርቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሐይማኖት መሪዎች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች የመንግሥት ተቺዎች በዘፈቀደ ለረጅም እና ላልተወሰነ ጊዜ ያለክስ ታስረው እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን በፍትሃዊነት መፈጸም የሚገባቸው የፍትሕ ሂደቶች ስልታዊ በሆነ መልኩ መጣሳቸው መቀጠሉን አብራርተዋል። ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ በማኅበር የመደራጀት እና የመሰብሰብ መብት፣ ገለልተኛ ሚዲያ እና ትችት በመታፈኑም ኤርትራ ውስጥ ለዜጎች መብት ያለው ምህዳር ሙሉ ለሙሉ መዘጋቱ ተመልክቷል።

ልዩ ዘጋቢው አክለው በኤርትራ ባለሥልጣናት የሚፈጸመው የዜጎችን ተሳትፎ እና ወሳኝ የሆኑ ድምጾችን የማፈን ሂደት በመላው ዓለም በሚገኙ የኤርትራ ማኅበረሰብ አባላት ላይም እንደሚደርስ ለምክርቤቱ አስረድተዋል።

ባቢከር አክለው የኤርትራ ኃይሎች አሁንም በአንዳንድ የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል አካባቢዎች እንደሚገኙ ጠቁመው ፣ትግራይ ውስጥ ያለፍርድ ግድያ፣ አፈና፣ በግዳጅ መሰወር፣ የዘፈቀደ እስራት እና የግዳጅ ስራን ጨምሮ "የሰብአዊ መብቶች እና የዓለም አቀፍ ሰብአዊነት ሕግጋትን መጣስ ቀጥለዋል" ብለዋል።

"ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኤርትራን የመብት ጥሰት ሰለባዎች መተው የለበትም" በማለትም የኤርትራ መንግስት ማሻሻያዎችን ለማድረግ የሚያስችለው ርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG