ብሪክስ በመባል የሚታወቀውን የሃገራት የኢኮኖሚ ትብብር ቡድን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ በማስተናገድ ላይ ያሉት የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ በሀገራቱ መካከል በሚደረግ የንግድ ልውውጥ ብሄራዊ ገንዘባቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስችል አሰራር ለመፍጠር በመሥራት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ባለፈው የቡድኑ የጆሃንስበርግ ጉቤኤ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ለመተግበር ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑን የጠቆሙት ላቭሮቭ፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓትን ለማሻሻልና በጋራ ግብይት ወቅት ብሔራዊ ገንዘብን ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል።
ላቭሮቭ በጉባኤው መክፈቻ ላይ በቅርቡ በሄሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸውን ላጡት የኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲ እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አሚር አብዶላሂያን የአንድ ደቂቃ ፀሎት እንዲደረግ ጠይቀዋል። ከጉባኤው ጎን ለጎንም ከቻይናው አቻቸው አንግ ዪ እና ከግብፁ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳመህ ሹክሪ ተነጋግረዋል።
ብሪክስ የዓለም 40 በመቶ ሕዝብ የሚወክል ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርትም ከአንድ አራተኛ በላዩን የያዘ ቡድን ነው።
የብሪክስ ጉባኤ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተመልክቷል።
መድረክ / ፎረም