የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ተኩስ አቁም እንዲደረስ በመደረግ ላይ ያለውን ጥረት ለመቀጠል ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አቅንተዋል።
ብሊንከን ዛሬ ሰኞ ማለዳ ካይሮ የገቡ ሲሆን፣ በመቀጠልም ዛሬውኑ ወደ እየሩሳሌም እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።
ብሊንከን በካይሮ ከፕሬዝደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋራ በዝግ ስብሰባ የሚነጋገሩ ሲሆን፣ ሲሲ እና ብሊንከን ላለፈው አንድ ወር ተዘግቶ የቆየውንንና በከበባ ላይ ላለችው ጋዛ ዕርዳታ ለማድረስ ዋና መተላለፊያ የሆነው የራፋ ድንበር በሚከፈትበት ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩ ይጠብቃል።
ግብፅ ለእስራኤል እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ ዓረብ ሃገር ስትሆን፣ እ.አ.አ በ1979 የሠላም ስምምነት ተፈራርመዋል። የእስራኤልና የፍልስጤማዊያንን ባልሥልጣናት ስታደራድርም ቆይታለች፡፡
የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ከፈነዳ ወዲህ ብሊንከን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሲያቀኑ ለስምንተኛ ጊዜ ሲሆን፣ በአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሣምንት በፊት የቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይጥራሉ ተብሏል።
የቀረበው አዲስ ሃሳብ እስራኤል በጋዛ ሕዝብ ከሚበዛበት አካባቢ እንድትወጣና፣ ሐማስ ደግሞ ታጋቾችን እንዲለቅ የሚያስችል የስድስት ሣምንታት የተኩስ አቁም እንዲደረግ እንዲሁም ጊዜያዊ ተኩስ አቁሙ ግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ እስከሚያገኝ እንዲራዘም የሚጠይቅ ነው።
ብሊንከን በመቀጠል ወደ ዮርዳኖስ እና ቃጣር ያቀናሉ ተብሏል።
መድረክ / ፎረም