የኢራን የበላይ ጠባቂ ምክር ቤት፣ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ እና ሌሎች ሰባት ሰዎች በሄሊኮፕተር አደጋ ከሞቱ በኋላ፣ እኤአ ሰኔ 28 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲወዳደሩ፣ ወግ አጥባቂውን መስመር ይከተላሉ ያላቸውን የፓርላማ አፈ-ጉባኤ እና ሌሎች አምስት ሰዎችን ስም አፅድቋል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ በምርጫው እንዳይወዳደሩ ምክር ቤቱ በድጋሚ አግዷቸዋል፡፡
የምክር ቤቱ ውሳኔ የኢብራሂም ራይሲን ሞት ተከትሎ በሁለት ሳምንት ውስጥ የሚካሄደው ምርጫ በፍጥነት እንዲጀመር በር የከፈተ ነው ተብሏል፡፡
ስር ነቀል ለውጥ የሚደግፉ ሴቶችም ሆኑ የመብት ተሟጋቾች በምርጫው እንዲወዳደሩ አልተፈቀደላቸውም።
ከእጩዎቹ ገናና ስም ያላቸው በቅርቡ የፓርላማ አፈ-ጉባኤ ሆነው በድጋሚ የተመረጡት የ62 ዓመቱ መሀመድ ባገር ቃሊባፍ ቀደም ሲል እኤአ ከ2005 እስከ 2017 የቴህራን ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል ።
እ.ኤ.አ. በ2005 እና 2013 ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው ያልተሳካላቸው ሲሆን፣ እኤአ ከ2017 ምርጫ ራሳቸውን በማግለል ለሟቹ ፕሬዝዳንት ራይሲ የቅስቀሳ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የወግ አጥባቂው የበላይ ጠባቂ ምክር ቤት መሪ አያቶላ ካሚኒ በቅርቡ ቃሊባፍን እንደሚደግፉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
መድረክ / ፎረም