በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፍሎሪዳ ውስጥ ሶስት ሴቶች በሻርክ ተነከሱ


 በናቫሬ የውቅያኖስ ባህር ዳርቻ ፣ ፍሎሪዳ እኤአ ማርች 27፣ 2013 (ፎቶ ፋይል)
በናቫሬ የውቅያኖስ ባህር ዳርቻ ፣ ፍሎሪዳ እኤአ ማርች 27፣ 2013 (ፎቶ ፋይል)

ዩናይትድ ስቴትስ ፎሎሪዳ ግዛት ውስጥ ከትላንት በስቲያ ዓርብ አንዲት ሴትና ሁለት ልጃገረዶች ላይ ሻርክ ጉዳት ማድረሱ ከተሰማ ወዲህ ባለሥልጣናት የውቅያኖሱን የባህር ዳርቻ እየጠበቁ ሲሆን ዋናተኞችንም አስጠንቅቀዋል፡፡

ሶስቱ ሰዎች ላይ የደረሰው የሻርክ ጉዳት በተመሳሳይ ቀን ቢሆንም ሁለት የተለያዩ ቦታዎች መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከአደጋው ጋር በተያያዘ በፍሎሪዳ ሰርጥ ውስጥ ያሉ በርካታ የባህር ዳርቻዎች ባላፈው ዓርብ አርብ ለዋናተኞች ተዘግተው ቆይተዋል፡፡

ትላንት ቅዳሜ ከፍተኛ የአደጋ ምልክቶችን ከሚያውለበልቡ ማስጠንቀቂያዎች ጋር ክፍት ተደርገዋል፡፡

በፍሎሪዳ ሳራሶታ፣ የሞቴ ማሪን ላቡራቶሪ እና በአኳይረም ቤተ ምርምር የሻርክ ጥናት ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ዴማን ቻፕማን “ማለት የምችለው እንዲህ ያለው አደጋ ከስንት አንዴ የሚገጥም ነው፡፡ በአንድ ቀን ሶስት ሰዎች ላይ የደረሱ ሁለት አጋጣሚዎችን መመልከቱ ደግሞ የበለጠ እንግዳ ነገር ነው” ብለዋል፡፡

በባህር ዳርቻው አቅራቢያ የሚጓዙ ትናንሽ ዓሦች ለሻርክ ጥቃቶች አስተዋፅዖ ያደርጉ ይሆናል ሲል የቤይ ካውንቲ ሸሪፍ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የመጀመሪያው ጥቃት የተፈፀመው ዎተር ሳውንድ ቢች (WaterSound Beach) ተብሎ በሚጠራው አቅራቢያ ነው፡፡

በአደጋው መካከለኛው የእጇ ክፍል ከባድ ጉዳት ያጋጠማት አንዲት ሴት የተወሰነ የእጇ ክፍል እንዲቆረጥ መደረጉን የሳውዝ ዋልተን እሳት አደጋ ክፍል ኃላፊ ራየን ክሮፎርድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ይህ ጉዳት ከደረሰ ሁለት ሰዐታት በኋላ 6.4 ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ሻርክ ሌላ አደጋ በሁለት ልጃገረዶች ላይ ማድረሱ ሪፖርት እንደደረሰው ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ከጓደኞቻቸው ጋር ሲዋኙ በነበሩ ልጃገረዶቹ ላይ መጠነኛ ነው የተባለው አደጋ የደረሰው ከወገብ በላይ በከፊል መቆም የሚያስችል ጥልቀት ባለው የውሃው ክፍል ውስጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጉዳቶቹን ያደረሰው አንድ ሻርክ ነው ወይስ ሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች ናቸው የሚለው እስካሁን አልታወቀም፡፡

በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ያሉ ሻርኮች ከዓመታት ቆይታ ወዲህ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል።

ሻርኮች በማለዳ እና በመሸ ጊዜ ስለሚመገቡ ከሰአት በኋላ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማየት ያልተለመደ እንደነበር ተገልጿል።

የሻርክ ጥቃቶች በዙም ያልተለመዱ ሲሆን ባላፈው ዓመት በመላው አለም 69 ንክሻዎች ሲደርሱ ከዚህ ውስጥ ለሞት የዳረጉት 10 እንደነበሩ ባለሙያዎች አስታውቀዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG