በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል 4 ታጋቾችን አስለቀቀች 274 ፍልስጤማውያን ተገደሉ


በእስራኤል ጦር ጥቃት የደረሰባቸው ፍልስጤማውያን
በእስራኤል ጦር ጥቃት የደረሰባቸው ፍልስጤማውያን

እስራኤል ዛሬ እሁድ ጋዛ ላይ "የነፍስ አድን ዘመቻ" ስትል በጠራችው ጥቃት አራት ታጋቾችን ያስለቀቀች ሲሆን፣ በጋዛ ሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደግሞ፣ በጥቃቱ በትንሹ የ274 ፍልስጤማውያን ህይወት ማለፉን አስታወቋል።

የነፍስ አድን ዘመቻው የተፈፀመው በአል-ኑሴራት፣ ጥቅጥቅ ባለው የመኖሪያ ሰፈር ሲሆን፣ የእስራኤል ሃይሎች ከፍተኛ ተኩስ በመክፈት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ተዘግቧል፡፡

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ "ሁሉም ታጋቾች እስኪለቀቁ ድረስ እስራኤል ተልዕኮዋን እንደምትቀጥል" አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የነፍስ ማዳኑ ዘመቻ "እጅግ ጀግንነት የተሞላበትና በ47 ዓመታት ቆይታዬ ካየሁት ጀብድ አንዱ ነው" ሲሉ ገልፀውታል።

የጤና ባለሥልጣናት ይህ እልቂት ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከነበሩት ደም አፋሳሽ ክስተቶች አንዱ ነው ብለውታል።

የጋዛ ጤና ባለስልጣናትም የሟቾች ቁጥር ከ210 ወደ 274 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡

የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የጦር አውሮፕላኖች ወደ መኖሪያ ቤቶች እና ለመሸሽ በሚሞክሩ ሰዎች ላይ ያለ ምንም ልዩነት መተኮሳቸውን የተመለከቱ የአይን እማኞች ጥቃቱን ከፍተኛ እልቂት ነው ብለውታል።

በስፍራው የወረደው የቦምብ ጥቃት በአካባቢው የገበያ ቦታ እና በአል-አውዳ መስጊድ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

የሐማስ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬ ተቃውሟቸው እንደሚቀጥል የገለፁ ሲሆን የአልቃሳም ብርጌድ ቃል አቀባይ በበኩላቸው በድርጊቱ ታጋቾች ተገድለዋል ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የታጋቾቹን መመለስ በደስታ ተቀብለው በእስራኤል እና በሂዝቦላ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እና ቀጠናዊ ግጭትን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ባይደን ሁሉም ታጋቾች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እና የተኩስ አቁም ጥረቱን እንደሚቀጥሉበት ቃል የገቡ ሲሆን፣ ዋይት ሀውስ ከተለያዩ አለም አቀፍ አካላት በሚገኘው ድጋፍ የአሜሪካ ዜጎችን ጨምሮ ቀሪዎቹን ታጋቾች ለማስፈታት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ ሃማስ የተኩስ አቁም ሀሳብን እንዲቀበል ለሚደረገው ጥረት ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንደሚመለሱ ታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG