በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሰባት “አይቪ ሊግ” ትምህርት ቤቶች ተቀባይነት ያገኘው ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊ አዳጊ


በሰባት “አይቪ ሊግ” ትምህርት ቤቶች ተቀባይነት ያገኘው ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊ አዳጊ
please wait

No media source currently available

0:00 0:10:07 0:00

በሰባት “አይቪ ሊግ” ትምህርት ቤቶች ተቀባይነት ያገኘው ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊ አዳጊ

ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊው አዳጊ ወጣት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአስደናቂ ውጤት በማጠናቀቅ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ክብር በሚሰጣቸው ሰባት “አይቪ ሊግ” ትምህርት ቤቶች ተቀባይነት አግኝቷል - ሃርቫርድ፣ ዬል፣ ፕሪንስተን፣ ኮሎምቢያ፣ ብራውን፣ ኮርኔል እና ፔንሲልቫንያ ዩንቨርስቲ።

ዩንቨርስቲዎቹ ውሳኔያቸውን ባሳወቁበት ቀን ኤታን ኮምፒውተሩ ፊት ተቀምጦ የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ "ሁሉም አይቪ ሊግ ትምህርት ቤቶች ውጤት የሚያሳውቁት በአንድ ቀን ነው። ከዛ በፊት የሌሎቹን ኮሌጆች ውጤት አውቄ ስለነበር የእነሱንም ውጤት ለማወቅ ጓጉቼ ነበር። እየከፈትኩ እያለሁ ውጤቱ በዚህ መልኩ ይኾናል ብዬ አልጠበኩም። ነገር ግን አንዱን ከፈትኩ እና ተቀብለውኛል ብዬ ተደሰትኩ። ከዛ ቀጥሎ ያለውን ስከፍትም ተቀብለውኛል። መጨረሻ ላይ የሆነውን ማመን አቅቶን ነበር" ይላል።

ከስመ ገናናዎቹ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ እንደ ጆርጅ ታውን እና ዲዩክ ዩንቨርስቲ የመሳሰሉ ሌሎች ከፍተኛ እውቅና ያላቸው አምስት የአሜሪካ ዩንቨርስቲዎችም ኤታንን ተቀብለውታል። የኤታን ምርጫ ግን ሃርቫርድ ዩንቨርስቲ በመሆኑ በመጪው አዲስ የትምህርት ዘመን የዩንቨርስቲውን ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል ይቀላቀላል። የወደፊት ህልሙ ደግሞ ሕግ ማጥናት ነው።

"ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ዩንቨርስቲውን ሄጄ ጎብኝቼ ነበር። ብዙ ተማሪዎችንም ተዋውቄያለሁ። በዩንቨርስቲው ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ እና ኤርትራውያን ማህበርም በጣም ደስ ይላል። እኔ ግን ከትምህርት ቤቱ በጣም የወደድኩት ውስጣቸው ያለውን ተነሳሽነት ነው። ያየኃቸው በሙሉ ትልቅ ዓላማ ያላቸው እና ትልቅ ቦታ ለመድረስ የሚጥሩ ናቸው። ዓለም ላይ ማሳካት የሚፈልጓቸው ትልልቅ ሀሳቦች አሏቸው። እኔ ደግሞ እራሴን በእንደነዚህ አይነት ሰዎች መክበብ ነው የምፈልገው። "

ይህ ብቻ አይደለም። ኤታን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ ኮሌጅ ከመግባታቸው በፊት የሚፈተኑን የትምህርት ብቃት መለኪያ (ኤስኤቲ) ፈተና 1ሺሕ 600 በማግኘት የመጨረሻውን ከፍተኛ ውጤት ካገኙ እንደ የፌስቡክ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ ያሉ ጥቂት ግለሰቦች መካከል አንዱ መሆንም ችሏል። በዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ ፈተናውን ከሚወስዱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተፈታኞች ውስጥ ከፍተኛውን ውጤት የሚያስመዘግቡት አንድ ከመቶ የሚኾኑ ተማሪዎች ብቻ ናቸው።

"በፈተና ክፍሉ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት፣ እንዴት እንደምገልፀው አላውቅም፣ ግን ጥሩ ስሜት ይሰማኝ ነበር። ለየት ያለ ስሜት ነው።" የሚለው ኤታን "ከፈተናው በፊት አስቀድሜ ብዙ ልምምድ አድርጌያለሁ። በኢንተርኔት ላይ ማግኘት የቻልኩትን ብዙ የሙከራ ፈተናዎች ሰርቻለሁ። ጠዋትም፣ ማታም፣ ትምህርት ቤት ከመሄዴ በፊትም፣ ቅዳሜ እና እሁድም፣ በቃ ባገኘሁት ጊዜ ሁሉ የሙከራ ፈተናዎችን እወስዳለሁ። ነገር ግን ዋና ፈተናውን የወስድኩ ቀን በቃ ጥሩ ስሜት ነበረኝ። አባቴ ከፈተናው ቦታ ሊወስደኝ ሲመጣ እና እንዴት ነበር ፈተናው ሲለኝ 1600 የማገኝ ይመስለኛል አልኩት። ስቀልድ ይሁን ወይም ታውቆኝ ይሁን አልውቅም። ግን ብዙ ጊዜ ለራሴ ከፍ ያለ ግብ አስቀምጣለሁ። በኃላ ውጤቱን ሳገኘው ግን ማመን አልቻልኩም" ሲል ስሜቱን ይገልጻል።

ከሁለት አስርት አመታት በፊት ወደ አሜሪካ ከመጡ ኢትዮጵያዊ ወላጆቹ የተወለደው የ18 ዓመቱ ታዳጊ ኤታን ያገኘው ስኬት የልፋታቸው ዋጋ መሆኑን አባቱ አቶ ፍፁም ርስቱ ይናገራሉ።

ኤታን በተወለደበት ወቅት እናቱ የኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ፣ አባቱ ደግሞ በጤና ኢንዱስትሪው የሜዲካል ኢሜጂንግ ተማሪዎች ነበሩ። በዚህ ምክንያት ዘወትር ከንባብ እና ከጥናት የማይለዩትን እናትና አባቱን እያየ ያደገው ኤታን ለትምህርት ፍቅር ያደረበት ከልጅነቱ ጀምሮ መሆኑን ነው አባቱ የሚገልጹት።

የኤታን ስኬት በትምህርቱ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። በትምህርት ቤቱ የመሰናክል ሩጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ጥሩ ውጤቶችን አግኝቷል። በትምህርት ቤቱ ኦርኬስትራ ውስጥም ቫዮሊን ይጫወጣል። የትምህርት ቤቱ የጥቁር ተማሪዎች ማህበር እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ክለብ ውስጥ ፕሬዝዳንት ነው። የትምህርት ቤቱን ለስደተኞች መብት የሚያቀነቅን ቡድን በመመስረት እስከ አሜሪካ ምክርቤት ድረስ ሄዶም ተሟግቷል። ከትምህርት ቤቱ ውጪ ደግሞ በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን እና በማህበረ ቅዱሳን ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ከሚያገለግላቸው ተግባራት በተጨማሪ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጥምረት ለትምህርት በተሰኘ ተቋም ስር ተማሪዎችን ያስጠናል። ኤታን እነዚህን ሁሉ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ማስኬድ የቻልኩት ጊዜዬን በአግባቡ ስለምጠቀም ነው ይላል።

"እኔ በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ውስጥ የምሳተፈው የሚያስደስቱኝ ነገሮች ብዙ በመሆናቸው ለው። ለምሳሌ በአብዛኛው የሁለተኛ ድረጃ ትምህርት ቆይታዬ እሮጥ ነበር፣ ምክንያቱም መሮጥ እወዳለሁ። ሙዚቃ ስለምወድ ቫዮሊን እጫወታለሁ። የውጭ ክስተቶች እና የዓለም ጉዳዮችን ማወቅ ስለምፈልግ ደግሞ የትምህርት ቤታችንን ዓለም አቀፍ ከለቦች እመራለሁ። የጥቁር ተማሪዎች ጉዳይ ስለሚስበኝም የጥቁር ተማሪዎችን ማህበር እመራለሁ። የስደተኞች የተግባር ቡድን ያቋቋምኩት ደግሞ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ስለሆን ነው፣ በተለይ ወላጆቼ ስደተኛ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የአቅሜን መርዳት እፈልጋለሁ። ይሄ ደግሞ ዩንቨርስቲ ስናመለክትም ይጠቅማል። ኮሌጆች ሙሉ ስብዕና ያላቸው፣ ስለማህበረሰባቸው የሚጨነቁ እና ከክፍል ውጪም ተሳትፎ ያላቸው ተማሪዎችን ይፈልጋሉ።"

ኤታን ለስኬቱ ትልቁን ድርሻ የሚሰጠው ለቤተሰቦቹ፣ በተለይ ደግሞ ለወላጆቹ ሲሆን አባቱም የወላጅ ክትትል ለልጆች ስኬት ትልቅ ቦታ እንዳለው በልጃቸው ማየታቸውን ነው የሚገልጹት።

ወቅታዊ ጉዳዮችን በንቃት የሚከታተለው ኤታን በሃርቫርድ ቆይታው ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን እና መንግስታዊ አስተዳድርን ያጠናል። አንድ ቀን ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኖ ሊመረጥ ይችላል የሚለው ሀሳብም ከብዙ ቦታ ይሰነዘርለታል።

"ብዙ ሰው የሚጠይቀኝ ጥያቄ ነው። የማደርጋቸውን ነገሮች የማደርገው አላማዬ እሱ ሆኖ አይደለም። ምናልባት አንድ ቀን የመንግስት ስልጣን ልይዝ እችላለሁ። ወይ ፖለቲካ ውስጥ እገባለሁ። ከሆነ ጥሩ እድል ነው። ነገር ግን ያለፉትን አራት አመታት ፊቴ ላይ ባለው ነገር ላይ ነው ያተኮርኩት። እድሉን ካገኘሁ ግን በእርግጠኝነት በደስታ እቀበለዋለሁ።"

ኤታን በአንድ ነገር ግን በጣም እርግጠኛ ነው። በሚኖርበት ህብረተሰብ አሉታዊ ተፅእኖ ፈጣሪ መሆን ይፈልጋል። ለማህበረሰቡ ወኪል መሆን እና ከዚህ በፊት ድምፃቸው ባልተወከለበት ቦታ ላይ ድምፅ ሆኜ የምሟገትላቸው ሰው መሆን እፈልጋለሁ ይላል።

"እየሆነ ባለው ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ። በጣም ብዙ እድል አለ። ብዙ የሚሰራ ነገር እንዳለ እና ብዙ ልጠቀምባቸው የምችላቸው ነገሮች እንዳሉም ይሰማኛል። ትምህርት እስኪጀመር፣ ወደ ኮሌጅ እስከምዬድ ቸኩያለሁ። አሁን ግን በዙሪያዬ እየሆነ ላለው ነገር በጣም አመስጋኝ ነኝ። የሚቀጥለውን ለማየት ደግሞ ጓጉቻለሁ።"

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG