በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሆነ


የእነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሆነ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:20 0:00

የእነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሆነ

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማዘዋወር በመሞከር ተጠርጥረው የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ በተመሠረተባቸው እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡

የዋስትና ጥያቄውን ያልተቀበለው ችሎቱ፣ በተከሳሾች የክስ መቃወሚያ እና በዐቃቤ ሕግ ምላሽ ላይ ለመበየን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ፣ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማውጣት ሙከራ አድርገዋል በሚል ከተከሰሱ አምስት ግለሰቦች መካከል፣ አንደኛ ተከሳሽ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንንና ሁለተኛ ተከሳሽ ኢያሱ እንዳለ፣ ባለፈው ሳምንት በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የተቀጠረው የዛሬ ችሎት ዋስትናውን አልተቀበለም።

የተከሳሾች ጠበቆች እና ዐቃቤያነ ሕግ በዋስትናው ጥያቄ ላይ ክርክር ያደረጉት፣ ባለፈው ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር፡፡

ጠበቆች፥ ክሱ ከሙስና ወንጀል ዐዋጅ ድንጋጌ ጋራ የማይጣጣም እንደኾነና በዐዋጁ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት፣ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል የሚያካትተው የመንግሥት ወይም የሕዝብ ድርጅት ሠራተኞችን ነው፤ ብለው ተከራክረዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ ማንኛውም ግለሰብ፣ ከባድ የማታለል ወንጀል ከፈጸመ ዋስትና የሚያስከለክል ክስ እንደሚመሠረትበት ያስረዱልኛል ያላቸውን የዐዋጁንና የወንጀል ሕጉን ድንጋጌዎች ጠቅሶ ተከራክረው ነበር፡፡

ዛሬ ሰኞ፣ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. የዋለው ችሎት፣ የዐቃቤ ሕግን መከራከሪያ ተቀብሎ ዋስትናውን ውድቅ አድርጓል፡፡ ችሎቱ ለውሳኔው ያቀረበውን ምክንያት ያስረዱት ከሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ ጠበቆች አንዱ አቶ ገብሩ ማኅተመ ሰይፉ፣ ውሳኔው የተሰጠው በሁለት ዳኞች መኾኑንም አስረድተዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ፣ ባለፈው ሳምንት በአንደኛ እና ሁለተኛ ተከሰሾች ለቀረበው የክስ መቃወሚያም የጽሑፍ ምላሽ አቅርቧል፡፡

ሦስተኛው ተከሳሽ ደግሞ፣ በጠበቆቻቸው አማካይነት የክስ መቃወሚያ በዛሬው ዕለት አቅርበዋል፡፡

ችሎቱ፣ በሦስቱ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያና በዐቃቤ ሕግ መልስ ላይ ብይን ለመስጠት፣ ለፊታችን ግንቦት 29 ቀን ቀጥሯል፡፡

አራተኛ እና አምስተኛ ተከሳሽ፣ ዛሬም ችሎት አልቀረቡም፡፡ ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርባቸው፣ ካላገኛቸውም ከሚኖሩበት ወረዳ በጽሑፍ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ችሎቱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG