ምስራቅ እየሩሳሌም የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የርዳታ ድርጅት ለፍልስጤማውያን ዋና መሥሪያ ቤት በቃጠሎ ጥቃት ምክኒያት ዘጋ። የእስራኤል ነዋሪዎች በተንጣለለው የድርጅቱ ግቢ ጠርዝ ላይ ያሉትን አካባቢዎች በእሳት ካቀጣጠሉ በኋላ ቢሮው መዘጋቱን ድርጅቱ አስታውቋል።
ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሐሙስ ጥቃት ሁለተኛው መኾኑን በ"ኤክስ" ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት የድርጅቱ ኃላፊ ፊሊፕ ላዛሪኒ፣ “ተገቢው የፀጥታ ጥበቃ እስካልተመለሰ ድረስ ድርጅቱ ግቢውን ለመዝጋት መወሰኑን” ተናግረዋል። "ይህ አስከፊ ርምጃ ነው።” ያሉት ኃላፊው “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞች ህይወት አሁንም ከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቋል" ብለዋል።
"የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች እና መገልገያዎች በማንኛውም ጊዜ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አካባቢውን የተቆጣጠረው የእስራኤል መንግሥት ኃላፊነት ነው” ሲሉም ላዛሪኒ ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች እና መገልገያዎች በማንኛውም ጊዜ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አካባቢውን የተቆጣጠረው የእስራኤል መንግሥት ኃላፊነት ነው”
የተባበሩት መንግሥታት የርዳታ እና ሥራዎች ተቋም ለፍልስጤም ስደተኞች፣ እ.ኤ.አ. በ1948፣ እስራኤል በተመሰረተችበት አካባቢ በነበረው ጦርነትና፣ ለረጅም ጊዜ የእስራኤል ጥቃት ኢላማ ሆነው ቤታቸውን ለቀው የወጡ ፍልስጤማውያን ስደተኞችን ለመርዳት የተፈጠረው ነው።
የእስራኤል ፖሊስ፣ በድርጅቱ ቅጥር ግቢ አጠገብ በተፈጸመው የቃጠሎ ጥቃት ላይ፣ ምርመራ መጀመሩን ተናግሯል። "በፖሊስ ምርመራ የመጀመሪያ ግኝቶች፣ ድርጊቱ የተፈፀመው በወጣት ታዳጊዎች ሲሆን፣ ይህም በወንጀል ተጠያቂነት ከተቀመጠው የእድሜ ገደብ በታች ነው ተብሎ ይገመታል" ብሏል፡፡
የጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ የእስራኤል ባለሥልጣናት የርዳታ ተቋሙ በጋዛ ከሚገኘው ሃማስ እስላማዊ እንቅስቃሴ ጋራ ተባባሪ ነው በሚል እንዲዘጋ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባለሥልጣናቱን ክስ አበክሮ ተቃውሞታል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
መድረክ / ፎረም