በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል አሜሪካ አንዳንድ የጦር መሳሪያ መላክ ለማቆም መወሰኗን ተቃወመች


የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ንብረታቸውን ሸክፈው ራፋህ ወደሚገኝ ደህንነቱ የተጠበቀ ሥፍራ ሲሸሹ እአአ ግንቦት 9/2024
የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ንብረታቸውን ሸክፈው ራፋህ ወደሚገኝ ደህንነቱ የተጠበቀ ሥፍራ ሲሸሹ እአአ ግንቦት 9/2024

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ እስራኤል ይላኩ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች በጊዜያዊነት እንዲቆሙ መወሰናቸውን የእስራኤል ባለሥልጣናት ተቃውመዋል። ባይደን ውሳኔውን ያሳለፉት እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻዋን ወደ ራፋህ ለማስፋት እቅድ በመያዟ ሲሆን፣ ዩናይትድ ስቴትስ እቅዱን አትደግፍም።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን የአሜሪካን ውሳኔ ተቃውመው በሰጡት አስተያየት "ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባደረጉልን ድጋፍ ስናመሰግናቸው ከነበሩ ፕሬዚዳንት ለመስማት አስቸጋሪ እና አሳዛኝ መግለጫ ነው" ብለዋል።

ቀኝ አክራሪ የሆኑት የእስራኤል ብሔራዊ የደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጊቪር በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክትም "ሐማስ ባይደንን ይወዳቸዋል" ብለዋል።

ባይደን ከሲኤንኤን ጋራ ባደረጉት እና ረቡዕ ምሽት በተላለፈው ቃለመጠይቅ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እንደ አየር መቃወሚያ ያሉ የመከላከያ መሳሪያዎችን ግን ለእስራኤል ማቅረብ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

ባይደን አክለው፣"እስካሁን ወደ ራፋህ አልሄዱም። ወደ ራፋህ የሚሄዱ ከሆነ ግን፣ በታሪክ ከራፋህ ጋር ያለውን ችግር፣ ከከተማው ጋራ ያለውን ሁኔታ እና ያንን ችግር ለመፍታት ጥቅም ላይ የሚውለውን የጦር መሳሪያ እንደማልሰጥ በግልፅ ተናግሬያለሁ" ብለዋል።

የባይደን ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት በራፋህ "ሐማስን ለመከላከል ከሌሎች የጋዛ አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ እንዴት መንቀሳቀስ እንደሚቻል" ከእስራኤል ጋር ውይይት ተደርጎ እነደነበር አንድ ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የአስተዳደሩ ባለስልጣን ለአሜሪካ ድምፅ በላኩት መግለጫ አስረድተዋል።

በጥቅምት ሰባት ሐማስ የሽብር ጥቃት ካደረሰ ወዲህ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በእስራኤል የጦር አካሄድ ላይ ተጽእኖ ለማድረግ የምትልከውን የጦር መሳሪያ እንደመያዣ ስትጠቀምበት የመጀመሪያ ጊዜ ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG