በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ዩንቨርስቲዎች በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ተቃውመው የሚካሂዷቸው ሰልፎች ቅዳሜ እለትም ቀጥለዋል። በአንዳንድ ቦታዎች ከአድማ በታኝ ፖሊሶች ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት ተማሪዎች ሰልፉን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል የገቡ ሲሆን፣ በርካታ መምህራን የዩንቨርስቲዎቹ ፕሬዝዳንቶች የተቃውሞ ሰልፎቹን ለመበተን ፖሊስ መጥራታቸውን አውግዘዋል።
ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ፣ ኒው ዮርክ ግዛት በሚገኘው ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ድንኳን ተክለው ተቃውሞ እያካሄዱ ካሉ የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች ጋር ድርድር ማካሄዱን በቀጠለበት ወቅት፣ የዩንቨርስቲው አስተዳደር ምክርቤት የትምህርት ቤቱን አመራር የሚፈትሽ ግብረ ሃይል እንዲቋቋም ውሳኔ አሳልፏል። የዩንቨርስቲው አመራር ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ለመበተን ፖሊስ መጥራቱን ተከትሎ ግብግብ መፈጠሩ እና ከመቶ በላይ ሰዎች መታሰራቸው ይታወሳል።
በጋዛው ጦርነት ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በጨመረ ቁጥር፣ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የሚካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች፣ ትምህርት ቤቶች ከእስራኤል ጋር ያላቸውን የገንዘብ ትስስር እንዲያቋርጡ እና ግጭቱን እያባባሱ ነው ካሏቸው ተቋማት እንዲርቁ እየጠየቁ ናቸው።
አንዳንድ የአይሁድ ተማሪዎች በበኩላቸው ተቃውሞዎቹ ወደ ፀረ-ሴማዊነት በመሸጋገራቸው ወደ ዩንቨርሲዎቹ ለመግባት ፍርሃት እንዳደረባቸው ተናግረዋል።
ሰልፎቹን ለመበተን ሕግ አስከባሪዎች መጠራታቸው በመላው አሜሪካ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለእስር በመዳረጉ፣ በካሊፎርኒያ፣ ጆርጂያ እና ቴክሳስ ግዛት የሚገኙ ዩንቨርስቲ መምህራን በአመራሩ ላይ ባላቸው እምነት ዙሪያ ድምፅ እንዲሰጡ አነሳስቷቸዋል። ድርጊቱ የዩንቨርስቲዎቹን ፕሬዝዳንቶች ከስልጣን ባያስነሳቸውም፣ ተምሳሌታዊ እርምጃ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
መድረክ / ፎረም