በዓለም ዙሪያ በግጭቶች፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በምጣኔ ሐብት ማሽቆልቆል የተነሳ ለአእጣዳፊ የረሃብ ችግር የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አንድ አዲስ ግምገማ አመለከተ፡፡
ዓለም አቀፍ የረሃብ ይዞታን በሚመለከት የተካሄደው አዲስ ጥናት እንዳስታወቀው፣ የተጠቀሱት ችግሮች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ በ2030 ዓመተ ምሕረት ረሃብን ለማስወገድ ያወጣውን ዕቅድ ለማሳካት ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ስራዎችን እያበላሸ መሆኑ ጠቁሟል፡፡
የ2024 የዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ ሪፖርቱ ዛሬ ረቡዕ የወጣ ሲሆን የምግብ ቀውስ ውስጥ ባሉ 59 ሀገሮች እና ግዛቶች ባለፈው 2023 ዓ.ም 281 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች ለአጣዳፊ የምግብ ዋስትና ችግር የተጋለጡ ሆነው አግኝቷቸዋል፡፡ አሃዙ በግምገማው ከተካተቱት መካከል 21 ነጥብ 5 ከመቶውን የሚይዝ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት የምግብ እና ግብርና ድርጅት (ፋኦ) ዳይሬክተር ዶሚኒክ በርገን ጄኔቫ ላይ በሰጡት ቃል፣ አጣዳፊ የምግብ ዋስትና ችግር የምንለው፣ የሰዎችን ህይወት እና የኑሮ መተዳደሪያ ለአጣዳፊ አደጋ በሚዳርግ ደረጃ የከበደ ረሃብ ማለታችን ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በዚህ መጠን ያለ ረሃብ ወደከባድ ቸነፈር በማሽቆልቆል በስፋት የሰዎች ህልፈት ሊያስከትል ይችላል ሲሉም ጨምረው አስገንዝበዋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ባለስልጣን አስከትለውም ለከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከተጋለጡ ህጻናት ውስጥ 60 ከመቶው የሚኖሩት ለአጣዳፊ የምግብ ዋስትና ችግር የተጋለጡ በሆኑ 10 ሀገሮች ውስጥ መሆኑን ሪፖርቱ መጠቆሙን አውስተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች፣ በተለይም በጋዛ እና ሱዳን ውስጥ የምግብ ቀውሶቹ በከፍተኛ ደረጃ መባባሳቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
መድረክ / ፎረም