በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በኢትዮጵያና ኤርትራ የሰብአዊ መብት አያያዙ እንደከፋ ነው” - ዩኤስ  


“በኢትዮጵያና ኤርትራ የሰብአዊ መብት አያያዙ እንደከፋ ነው” - ዩኤስ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:46 0:00

“በኢትዮጵያና ኤርትራ የሰብአዊ መብት አያያዙ እንደከፋ ነው” - ዩኤስ

የዩናዩትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገራትን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በተመለከተ የሚያወጣውን ዓመታዊ ሪፖርት በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትላንት ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም ባወጣው የሃገራትን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በሚተነትነው ሰፊ የአውሮፓያኑ የ2023 ዓመታዊ ሪፖርቱ፤ ፣የኢትዮጵያ መንግሥት ወይም የመንግሥት ወኪሎች፣ ከሕግ ውጪ የዘፈቀደ ግድያ መፈፀማቸውን፣ በርካታ የሃገር ውስጥና የውጪ ሃገራት የሰብአዊ መብት ቡድኖች ሪፖርት ጠቅሶ ይፋ አድርጓል።

ግድያዎቹ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች እንዲሁም ትግራይን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙ እንደሆነ አስታውቋል።

የክልል ፖሊስ አባላትም ፣ ከመጠን ያለፈ እና ሕይወት የቀጠፈ ኃይል መጠቀማቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ለማሳያም፣ “በየካቲት ወር በወልቂጤ ከተማ የውሃ አገልግሎት እንዲመለስ በሰልፍ ለመጠየቅ በወጡ ነዋሪዎች ላይ በተወሰደው ርምጃ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ 30 የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብሏል። በሌሎችም አካባባዎች የተፈጸሙ ግድያዎችን ያካተተው ሪፖርት፣ የፌዴራሉ ፖሊስ ምርመራ ቢሮ በፖሊስ ኃይሎች የሚፈጸሙ ግድያዎችን በተመለከተ የሚያደርጋቸው ምርመራዎች ውስን መሆናቸውን እና የሚሰጠውን ቅጣት በተመለከተም በሚስጥር እንደሚይዝ ጠቁሟል።

በግዳጅ መሰወርን አስመልክቶም፣ መንግሥትን የሚነቅፉ የፖለቲካ አስተያየት የሚሰጡ ግለሰቦች፣ የቀድሞ ጦር አባላት፣ የምርመራ ጋዜጠኞች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች መሰወራቸውን አትቷል። መንግሥት በጋዜጠኞች እና አንቂዎች ላይ እስሩን ባጠናከረበትም ወቅት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣መንግሥት የተሰወሩትን ግለሰቦች በተመለከተ የት እንዳሉ እንዲያሳወቅና ለፍርድ መቅረብ ካለባቸውም አስተማማኝ ማስረጃውን እንዲያቀርብ በሰኔ ወር መጠየቁን አስታውሷል።

በአማራ እና በኦሮሚያ እየተካሄዱ ከነበሩ ግጭቶች ጋራ በተያያዘ፣ በግዳጅ መሰወር መበራከቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ አዲስ አበባንና ጂቡቲን በሚያገናኘው መንገድ የሚሠሩ ሾፌሮች መንግሥት የደህንነት ስጋታቸውን እንዲመለከት ጠይቀዋል ብሏል።

በሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች፣ ሪፖርቱ ሞዕራብ ትግራይ ሲል በጠራውና በአሁኑ ወቅት አማራ እና ትግራይ ክልል በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ተይዘው እንደሚገኙ ጠቁሟል።

በነሐሴ ወር በአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ አገልግሎት የቀረበውንና ‘ቅድሚያ ለሰብአዊ መብት’ የተሰኘ ቡድን 3ሺሕ የሚሆኑ የቀድሞ የመከላከያ አባላት የትግራይ ተወላጆች በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት እንደሚለቀቁ ተስፋ ቢደረግም ባልታወቀ ስፍራ ተይዘው እንደሚገኙ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ መ/ቤት በሪፖርቱ ጠቅሷል። ቪኦኤ ያነጋገራቸው የቤተሰብ አባላት፣ ሁኔታውን ከተለቀቁ እስረኞች እንደተረዱ ማስታወቃቸውንም አክሏል።

በመቐለ ከተማ የታሰሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአስከፊ ችግር ላይ እንደሚገኙ ገለጹ
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:13 0:00

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል፣ በሶማሌ እና በሌሎችም ክልሎች በሚገኙ እስረኞች ላይ መንግሥት ስቃይ እንደሚፈጽም፣ ስቃይን በተመለከተ የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ቡድንን ጨምሮ ኢሰመኮና ሌሎችም በሪፖርታቸው ማመልከታቸውንም ጠቅሷል።

በምዕራብ ትግራይ የተያዙ የትግራይ ተወላጆች በብረት፣ የኮረንቲ ሽቦ እና ዱላ ድብደባ እንደሚፈጸምባችውና ስቃይን በተመለከተ የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ቡድን ጉዳዩ እንዳሳሰበው መግለጹን አስፍሯል።

ከኃይማኖትም ሆነ ከሌሎች ጉዳዮች ጋራ በተያያዘ መንግሥት በርካታ የአማራ እና የኦሮሞ ተወላጆችን እንዲሁም ጋዜጠኞችን ከሕግ ውጪ እንዳሰረ፣ ሰባት የሚሆኑ ተቃዋሚ የኦሮሞ ተወላጆች በዘፈቀደ ለሦስት ዓመታት መያዛቸው፣ ይህም መንግሥት በተደጋጋሚ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን እና ተገቢ የሕግ ሂደትን በመጣሱ እንደሆነና ሂውማን ራይትስ ዋች በሰኔ ወር እስረኞቹ እንዲለቀቁ ጥሪ ማድረጉን ሪፖርቱ ይዘረዝራል።

በነሃሴ ወር ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ እና የተወካዮች ም/ቤት አባሉ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ ሌሎችንም፣ በአማራ ክልል ካለው ግጭት ጋራ በተያያዘ መታገታቸውን፣ ኢሰመኮም 53 እስረኞችን በአዋሽ አርባ ተገኝቶ መጎብኘቱን፣ ከእነዚህም ውስጥ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ም/ቤት አባሉ ዮሐንስ ቧያለው እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት አባሉ ካሳ ተሻገር እንደሚገኙበት፣ ግለሰቦቹም በምርጫ ክልላቸው ተይዘው ወደ አፋር ክልል እንደተወሰዱ፣ታሳሪዎቹም በአዋሽ አርባ ይደርስባቸው ስለነበረው ዘር ተኮር ስድብና ዛቻ ለኢሰመኮ መናገራቸውን፤ ሪፖርቱ አትቷል።

የችሎት ዘገባ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:15 0:00

በህወሃትና በመንግሥት መካከል የነበረው ግጭት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ቢቆምም፣ በአማራና በኦሮሚያ ሁከቱ መቀጠሉን፤ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ እና በኦሮሚያ በእቅድ የተፈጸመ ብሎ የገለታቸውና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የጣሱ ወንጀሎች መፈጸማቸውን፤ ከእነዚህ ውስጥም የጅምላ ግድያ፣ መደፈር፣ በረሃብ መቅጣት፣ በግዳጅ ማፈናቀል እና በዘፈቀደ ማሰር እንደተፈጸመ ዘርዝሯል።

የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ሚሊሺያ በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች በትግራይ ያለው ግጭት እንዳልቆመ፣ በተመድ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት የባለሞያዎች ቡድን ማስታወቁን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ዓመታዊ የሰብአዊ መብት ሪፖርት አስታውቋል።

በነሐሴ ወር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በፈጸመው የአየር ጥቃት በፍኖተ ሰላም፣ በባህር ዳር እና በሸዋ ሮቢት በጅምላ ሰዎች መገደላቸውን፣በዛው በነሐሴ ወር የጸጥታ ኃይሎች በቾቤ ወረዳ 12 ሲቪሎችን መግደላቸውን የኦሮሞ ፌዴራልሲት ለቪኦኤ አማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ማስታወቁን፣ ሌብነትን በተመለከተ በሁሉም ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናት የተሳፉበትና በተመድና በሌሎችም ለጋሾች የተላከ የርዳታ ምግብ ተዘርፎ ለገበያ መቅረቡንና ባለፈው መጋቢት መጋለጡን ሪፖርቱ አስታውሷል።

በጥቅምት ወር 2014 የሰላም ስምምነት ቢፈረምም፣ በኤርትራ ወታደሮችና በሚሊሺያ ቡድኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶች መቀጠላቸውን፣ የፌዴራል አገር መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የህወሃት ኃይሎች፣ እና የአማራ ኃይሎች በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ግጭት የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን፣ ከእንዚህም ውስጥ ግድያ፣ መደፈርና ሌሎች የጾታ ጥቃቶች እንደሚገኙበት ባለፈው መጋቢት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁን፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዓይነታቸው በርከት ያለ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በየዓመቱ መቀጠላቸውን ሪፖርቱ አውስቷል።

ኤርትራን በተመለከተ፣ ከቀደመው ዓመት አንጻር የተለየ ለውጥ እንደሌለ፤ የኤርትራ መከላከያ ኃይሎች ባለፈው መጋቢት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ግጭት የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ ግድያ፣ መድፈርና ሌሎች የጾታ ጥቃቶች መፈጸማቸውን፣በሀገሪቱ መንግሥት የግዳጅ መሰወር፣ ሰቆቃ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ኢሰብአዊ የሆነ አያያዝ መደረጉን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

አስቸጋሪና ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል የእስር ቤት ሁኔታ፣ በዘፈቀደ መያዝና መታሰር፣ የፍትህ አካላት ገለልተኛ አለመሆን፣ በፖለቲካ ምክንያት መታገት፣ በሌሎች ሀገራት በሚገኙ ኤርትራውያን ላይ የሚፈጸም ጭቆና፣ በሰዎች የግል ጉዳይ በሕገ ወጥ መንገድ ጣልቃ መግባት፣ አንድ የቤተሰብ አባል አጠፋ ለተባለው ሌላውን የቤተሰብ አባል መቅጣት፣ ከግጭት ጋራ የተያያዙ የጾታ ጥቃቶች፣ ሕጻናት በትጥቅ ግጭት እንዲሳተፉ በመንግስት መመልመል፣ በጋዜጠኞች ላይ ኢፍትሃዊ እስርን ጨምሮ በሚዲያ እና በግለሰቦች ላይ ሃሳብን የመግለጽ መብት መታፈን፣ በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብና የመደራጀት መብት እገዳ፣ በአገር ውስጥም ሆነ ወደ ወጪ ሀገራት በሚደረግ ጉዞ ላይ የተጣለ ገደብ፣ በፖለቲካ ተሳትፎ ላይ የተጣለ ጠንካራ ገደብ፣ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ሀገራት የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ላይ የተጣለ ገደብ፣ ዜጎች በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ መንግስታቸውን በሰላማዊ መንገድ መቀየር አለመቻል፣ የመሳሰሉት ጥሰቶች መቀጠላቸውን የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቲር ኤርትራን በተመለከተ ባካተተው ሪፖርት ላይ አመልክቷል።

በብሔራዊ ውትድርናም ሆነ በሚሊሺያ አገልግሉት ላለመሳተፍ ይፈልጋሉ ተብለው የተጠረጠሩ፣ መንግሥትን የሚተቹ፣ ካለ መውጪያ ቪዛ ከሃገር ለመውጣት ይሞክራሉ ወይም በግልጽ ያልተጠቀሰና የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ናቸው በሚል የተጠረጠሩ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የፀጥታ ኃይሎች እንደሚያግቱ፣በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ከ20 ዓመታት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እስር ላይ እንደሚገኙ፣ 500 የሚሆኑ የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ካለ ፍርድ ሂደት ታስረው እንደሚገኙ፣ባለፈው ሚያዚያ 103 የሚሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮች አሥመራ ውስጥ ተይዘው ወደ ማይ ሰርዋ እስር ቤት እንደተወሰዱ፣በሐምሌ ወር ከነበረ ተቃውሞ ጋራ በተያያዘ ተይዘው የነበሩ 300 የእስልምና ተከታዮች መለቀቃቸውን፣ ሪፖርቱ አትቷል።

በኤርትራ በሌሎችም ሁኔታዎች ውስጥ የሰብዓዊ መብትን የተመለከቱ ጥሰቶች እንደሚስተዋሉ ሪፖርቱ አመልክቷል። አድማጮች በዚህ ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ወደ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ደውለን፣ ምላሽ አላገኘንም። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥት ምላሽ እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG