በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የሰዎችን ደብዛ ማጥፋት መቆም እንዳለበት ኢሰመኮ አሳሰበ


በኢትዮጵያ የሰዎችን ደብዛ ማጥፋት መቆም እንዳለበት ኢሰመኮ አሳሰበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:07 0:00

በኢትዮጵያ የሰዎችን ደብዛ ማጥፋት መቆም እንዳለበት ኢሰመኮ አሳሰበ

በኢትዮጵያ፣ በመንግሥት አካል ወይም በአካሉ እውቅና የሰዎችን ደብዛ የማጥፋት ድርጊት መጨመሩን ያስታወቀው ኢሰመኮ፣ በአፋጣኝ መቆም እንዳለበት አሳሰበ።

ከኅብረተሰቡ የሚቀርቡ፣ ደብዛ የማጥፋት ወንጀል ጥቆማዎች፣ በየጊዜው መበራከታቸውን፣ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዲሬክተር ሰላማዊት ግርማይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ፣ ባለፉት ሁለት ወራት፣ ከዐዲስ አበባ ከተማ ብቻ፣ 11 “የአስገድዶ መሰወር” ጥቆማዎች፣ ለኮሚሽኑ እንደደረሱት ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአደረገው ክትትል እና ከፖሊስ ጋራ በመነጋገር፣ የተወሰኑ ሰዎችን ለማግኘት ቢቻልም፣ ያሉበት የማይታወቁ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል፡፡

በተጠቂዎቹ ላይ፣ በቀጥታ ከሚደርሰው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተጨማሪ፣ በቤተሰቦቻቸውም ላይ በርካታ ጉዳቶችን ማድረሱን የገለጸው ኢሰመኮ፣ ድርጊቱ በአፋጣኝ እንዲቆም አሳስቧል፡፡

ኢሰመኮ ስላቀረበው የደብዛ ማጥፋት ወንጀል የምርመራ ውጤት፣ ከፌዴራል መንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት እና ከፌዴራል ፖሊስ፣ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ፣ በእጅ ስልካቸው ላይ የደወልንላቸው ሓላፊዎች ስልካቸውን ባለማንሣታቸው ለጊዜው ሊሳካልን አልቻለም፡፡

የኢሰመኮ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ)፣ ዛሬ በአወጣው መግለጫ፣ የመሰወር እና ሰዎች ተይዘው የሚገኙበት ኹኔታ ሳይታወቅ በእስር ላይ የማቆየት ወንጀል፣ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ እንደመጣ አመልክቷል፡፡

ኢሰመኮ፣ በተለይ በዐዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያ እና በዐማራ ክልሎች ከደረሱት አቤቱታዎች እና ጥቆማዎች በመነሣት፣ አደረግኹት ባለው ክትትል መሠረት፣ “በርካታ የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶች መፈጸማቸውን አረጋግጫለኹ፤” ብሏል።

በመንግሥት አካል ወይም በአካሉ እውቅና፣ “አንድን ሰው በማሰር፣ አፍኖ በመውሰድ፣ ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ፣ ነፃነቱን በማጥፋት እና በቁጥጥር ሥር መዋሉን በመካድ፣ በመደበቅ፣ የአለበትን ቦታ ባለማሳወቅ ወይም ደብዛውን በማጥፋት፣ ፈጽሞ ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዲኾን በማድረግ’’ የሚገለጸው ይህ ድርጊት፣ እንዳሳሰበውም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ፣ ባለፉት ሁለት ወራት ከዐዲስ አበባ ከተማ ብቻ፣ 11 የአስገድዶ መሰወር ጥቆማዎች እንደደረሱት ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ፣ በሌሎች ክልሎችም ያሉ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን በማሳያነት አቅርቧል፡፡ ለአብነትም፣ “አንድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል፣ ‘ከሠራዊቱ ከድቷል’ በሚል በዐማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ወረብ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑትን ወላጅ አባቱን፥ ልጅህን አምጣ በሚል፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በግዳጅ ተወስደው ተሰውረው ከቆዩ በኋላ፣ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ተለቀዋል፤” ብሏል፡፡

አንድ የቀድሞ የሶማሊ ክልል ልዩ ኃይል አባል ደግሞ፣ ታኅሣሥ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ከቢሮ ተደውሎለት፣ ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሮ እንዲመጣ ተጠርቶ ከሔደ በኋላ፣ በዕለቱ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጅምሮ ስልኩ የተዘጋ ሲኾን፣ “ከዚያ ቀን ጀምሮ የት እና ምን ኹኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ አልተቻለም፤” ሲልም ኢሰመኮ አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል፣ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ ቦታዎች፣ ቢያንስ ሰባት ሰዎች፣ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ሰለባ ስለመኾናቸው አቤቱታ እንደቀረበለት፣ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ከእነዚኽም መካከል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ ነዋሪ የኾነ አንድ ግለሰብ፣ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሌሎች ሦስት ጓደኞቹ ጋራ በወረዳው ፖሊስ ተይዞ ፖሊስ ጣቢያ ከገባ በኋላ፣ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሌሎቹ ታሳሪዎች ተለይቶ፣ ነቀምት ከተማ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንደተዘዋወረ ለቤተሰብ ቢነገርም፣ ከዚያ ቀን ጀምሮ ያለበትን ቦታ እና ኹኔታ ማወቅ አልተቻለም፤ ሲል አብራርቷል፡፡

በተመሳሳይ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የምሥራቅ ወለጋ ዞን የኦፌኮ አስተባባሪ የኾነ ሌላ ሰው፣ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ፣ ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት፣ በመንግሥት የደኅንነት ኃይሎች ተይዞ፣ ነቀምት ከተማ በሚገኘው የጸጥታ ቢሮ ውስጥ ታስሮ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት እንደነበረና እጁ በሰንሰለት በመታሰሩ ምክንያት፣ ከቤተሰብ የሚሔድለትን ምግብ ተቀብሎ መመገብ አቅቶት እንደነበር፣ ከመረጃ ምንጮች ማወቅ ተችሏል፤ ብሏል ኮሚሽኑ። ግለሰቡ፣ ከጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሊገኝ እንዳልቻለም ጠቅሷል።

ኢሰመኮ፣ በሌሎች አንዳንድ አካባቢዎችም፣ የተፈጸሙ የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶችን በመግለጫው ያብራራ ሲኾን፣ ጉዳዩን በተመለከተ ለመንግሥት የጸጥታ አካላት ማሳወቁንና ንግግር መደረጉንም፣ የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ተናግረዋል፡፡

ኢሰመኮ፣ አስገድዶ የመሰወር ወንጀል እየጨመረ መቀጠሉን በተመለከተ ስላቀረበው የምርመራ ውጤት፣ ከፌዴራል መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና ከፌዴራል ፖሊስ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ፣ በእጅ ስልካቸው ላይ የደወልንላቸው ሓላፊዎች ስልካቸውን ባለማንሣታቸው ለጊዜው ሊሳካልን አልቻለም፡፡ የአሜሪካ ድምፅ በቀጣይ፣ የመንግሥትን ምላሽ ካገኘ ይዞ የሚቀርብ ይኾናል፡፡

ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው፣ በአስገድዶ መሰወሩ ወቅት ተፈጽሟል ስለተባለ ተገቢ ያልኾነ አያያዝ ወይም የሥቅየት ተግባር፣ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

XS
SM
MD
LG