በአሜሪካ የተወካዮች ም/ቤት ለዩክሬን እና ለእስራኤል የሚሰጥን የ95 ቢሊዮን ዶላር የዕርዳታ ጥቅል ሕግ ከወራት ሙግት በኋላ ትናንት ቅዳሜ አጽድቋል።
በኮንግረስ ያሉ መሪዎች ከቀኝ ዘመም ወግ አጥባቂዎች የደረሰባቸውን ተቃውሞ ወደ ጎን በማለት፣ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ቅዳሜ ዕለት በተገናኘው ም/ቤት ሕጉን እንዲጸድቅ አድርገዋል።
አሁን የቀረው ሕጉን ወደ ሕግ አውጪው ሸንጎ ወይም ሴኔቱ መላክ ሲሆን፣ በዲሞክራቶቹ ቁጥጥር ስር ያለው ሴኔት እስከ ማክሰኞ ድረስ እንደሚያጸድቀው ይጠበቃል።
ከፓርቲያቸው ከፍተኛ ግፊት ያላባቸው ሪፐብሊካኑ የም/ቤቱ አፈጉባኤ ማይክ ጆንሰን፣ ወንበራቸውን እንደሚያጡ በፓርቲያቸው አባላት ዛቻ እየደረሰባቸው ሲሆን፣ ሕጉን ለማጽደቅ በተደረገው እያንዳንዱ እርምጃ የዲሞክራቶቹን ዕገዛ አግኝተዋል ተብሏል።
አራት ክፍሎች ያሉት ሕግ፣ ለዩክሬን፣ እስራኤል እና በኢንዶ ፓሲፊክ ለሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች ገንዘብ የሚመድብ ሲሆን፣ ቲክ ቶክ በአሜሪካ ማኅበረሰብ ዘንድ ፈጥሯል የሚባለውንም ችግር የሚመለከት ነው።
ሕጉ በም/ቤቱ የሚጸድቅ ከሆነ፣ በፊርማቸው እንደሚያጸኑት ፕሬዝደንት ባይደን ሲያስታውቁ ቆይተዋል።
መድረክ / ፎረም