በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በእስራኤሉ የራፋ አየር ጥቃት 6 ህጻናትን ጨምሮ 9 ፍልስጤማውያን ሞቱ


በእስራኤሉ የአየር ጥቃት የቆሰለው ፍልስጤማዊው ታዳጊ በራፋ መጠለያ ካምፕ በሚገኝ ሆስፒታል (እኤአ ሚያዝያ 20 2024)
በእስራኤሉ የአየር ጥቃት የቆሰለው ፍልስጤማዊው ታዳጊ በራፋ መጠለያ ካምፕ በሚገኝ ሆስፒታል (እኤአ ሚያዝያ 20 2024)

በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ከተማ በደረሰ የእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያንስ 6 ህጻናትን ጨምሮ 9 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የሆስፒታል ባለሥልጥናት ዛሬ ቅዳሜ ተናገሩ፡፡

የጋዛ ሲቪል መከላከያ እንደገለፀው ትላንት አርብ ምሽት የተካሄደው ጥቃት በራፋህ ከተማ ምዕራባዊ ቴል ሱልጣን ሰፈር ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ጉዳት ደርሷል።

በጥቃቱ የሞቱ የስድስቱ ህጻናት፣ የሁለት ሴቶች እና የአንድ ወንድ አስከሬኖች ወደ ራፋህ አቡ ዩሱፍ አል-ናጃር ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሆስፒታሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል አብደል ፈታህ ሶቢ ራድዋን ፣ ባላቤታቸው ናጃላ አህመድ አዋይዳህ እና ሶስት ልጆቻቸው፣ እንደሚገኙበት የሟች ባለቤት ወንድም የሆኑት አህመድ ባርሆም ተናግረዋል፡፡

ባርሆም ራሳቸው ባለቤታቸውን ራዋን ራድዋን እና የአምስት አመት ሴት ልጃቸው አላ እንደተገደሉባቸው ገልጸዋል፡፡

የአምስ ዓመት ልጃቸውን አስክሬን ታቅፈው በሀዘን እየተወዘዙ የሚያለቅሱት ባርሆም "ይህ ዓለም ከሁሉም ሰብአዊ እሴቶች እና ስነምግባር የራቀ ነው" ሲሉ ዛሬ ቅዳሜ መናገራቸውን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ባርሆም አክለውም “ በተፈናቀሉ ሰዎች፣ በሴቶችና በህጻናት የተሞላውን ቤት በቦምብ አጋዩት፡፡ ሴቶችና ህጻናት እንጂ ሰማዕታት አልነበሩም” ማለታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

በግብፅ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘው ራፋህ በአሁኑ ጊዜ ወደ 2.3 ሚሊዮን ከሚጠጋው የጋዛ ህዝብ ወደ ግማሽ የሚጠጋውን ህዝብ ታስተናግዳለች፡፡ አብዛኞቹ ወደ ስሜን የሀገሪቱ ግዛት እየተስፋፋ ያለውን ጦርነት በመሸሽ ተፈናቅለው የመጡ ናቸው፡፡

የእስራኤል ጠንካራ አጋር የሆነችውን ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ ቢቀርብም የእስራኤል መንግሥት ከተረፉት ሀማስ ታጣቂዎች እጅግ የበዙት ይገኙበታል በሚለው ከተማ የሚያደርገውን የምድር ጥቃት እንደሚያካሂድ ለወራት ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

የተባለው የምድር ጥቃት እስካሁን ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ ይሁን እንጂ እስራኤል በከተማው እና አካባቢው ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት አካሂዳለች፡፡

ጦርነቱ የተቀሰቀሰው እኤአ ጥቅምት 7 ሃማስ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በደቡብ እስራኤል ታይቶ የማይታወቅ የወረራ ጥቃት በመፈጸማቸው ነው፡፡

በዚሁ ጥቃት አብዛኞቹ ሲቪሎች የሆኑ ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ወደ 250 የሚጠጉ ሰዎች ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል። ምንም እንኳን ጥቅምት 7 ተገድለዋል ወይም በግዞት ህይወታቸው አልፏል የተባሉ ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ቢሆንም፣ አሁንም 130 የሚጠጉ ታጋቾች በጋዛ እንደቀሩ እስራኤል ተናግራለች፡፡

የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ ቅዳሜ እንዳስታወቀው በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት የ37 ሰዎች አስከሬን እና 68 ቁስለኞች ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ወደ ጋዛ ሆስፒታሎች ገብተዋል።

በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት የሞቱት ፍልስጤማውያን 34,049 ሲሆኑ የቆሰሉት ደግሞ 76,901 መድረሱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ምንም እንኳን በሃማስ የሚተዳደሩት የጤና ባለስልጣናት ቁጥራቸው ውስጥ በተፋላሚዎች እና በሲቪሎች መካከል ያለውን ልዩነት ባይገልጹም፣ ቢያንስ ሁለት ሶስተኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች ናቸው ይላሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG