እስራኤል ኢራን ውስጥ በአገሩ ሰዓት ዛሬ ዓርብ ሌሊት ላይ የአየር ጥቃት ማድረሷን የዩናይትድድ ስቴትስ የብዙሃን መገናኛዎች በስም ያልጠቀሷቸውን የዩናይትድ ስቴስ እና የእስራኤል ጋዜጦች ጠቅሰው ዘገቡ።
ሌሊት ላይ የተካሄደው ጥቃት፣ በሁለቱ የመካከለኛው ምስራቅ ባላንጣዎች መካከል በቅርቡ ከተካሄዱት የመበቃቀል ጥቃቶች የኋለኛው ሲሆን ቴህራን የዛሬውን የእስራኤል ጥቃት አክብዳ አልተመለከተችውም። አጸፋ የመመለስ ዕቅድ እንደሌላትም ፍንጭ ሰጥታለች።
ኒው ዮርክ ታይምስ እና ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጦች ባወጧቸው ዘገባዎች እስራኤል ኢራን ላይ የአየር ድብደባ ማድረሷን የእስራኤል ባለሥልጣናት እንደተናገሩ አመልክተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት እስራኤል ኢራን ላይ የሚሳይል ጥቃት አድርሳለች ማለታቸውን በርካታ የዜና ማሰራጫዎች ዘግበዋል።
ጥቃቱ በየትኛው የኢራን አካባቢ ላይ እንደተፈጸመ አልተገለጸም። ዘገባዎቹ ከወጡ ከአንድ ሰዓት በኋላ ቪኦኤ ስለጉዳዮ የጠየቃቸው የእስራኤል የጦር ኃይል ቃል አቀባይ "ለጊዜው የምሰጠው አስተያየት የለም" ብለዋል። የባይደን አስተዳደርም ስለጉዳዩ በይፋ አስተያየት አልሰጠም።
ኢርና እና ፋርሲ የተባሉት የኢራን መንግሥት የዜና አገልግሎቶች በማዕከላዊ ኢራኗ ኢስፋሃን ከተማ አካባቢ ላይ መተኮሱን ተከትሎ የኢራን የአየር መከላከያ ኃይሎች በተጠንቀቅ ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል። በከተማዋ በስተምስራቅ አካባቢውም ፍንዳታ መሰማቱን ገልጸዋል። ፍንዳታው ከአየር ጥቃት መከላከያ ተኩስ ይሁን ወይም ወደመሬት ላይ ካረፈ ፈንጂ ይሁን ለይተው አልተናገሩም።
የኢራን የጠፈር ድርጅት የአየር መከላከያ ኃይሎች በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትተው ጥለዋል ሲል ተናግሯል።
የኢራን መንግሥት የዜና ማሰራጫዎች ኢስፋሃን የሚገኙት የኒውክሊየር ጣቢያዎች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም በማለት ጥቃቱን ፈጥነው አጣጥለዋል። የቴህራን ኢማም ኾሚኒ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያ እና ሜህራባዳድ ከተማ ያለው የአገር ውስጥ አውሮፕላን ጣቢያ ደርሷል የተባለውን የአየር ጥቃት ተከትሎ ተቋርጠው የነበሩት በረራዎች መቀጠላቸውን አመልክተዋል።
በእስራኤል እና በኢራን መካከል ለአንድ ዓመት ያህል በይፋ ሳይገለጽ የዘለቀው ግጭት ከሰሞኑ ተባብሷል። ኢራን ባለፈው ዕሁድ በእስራኤል ግዛት ላይ በብዙ መቶ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳይሎች ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ እስራኤል አጸፋ እንደምትመልስ አስጠንቅቃለች። የተተኮሱትን ሚሳይሎች በሙሉ በሚባል ደረጃ በምዕራባዊያን ሀገሮች እና አጋሮቿ በሆኑ የአረብ ሀገሮች ርዳታ መትታ መጣሏን መናገሯ ይታወሳል።
መድረክ / ፎረም