የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ትረምፕ’ን የወንጀል ክስ ጉዳይ የሚያዩት የኒው ዮርኩ ዳኛ ዛሬ ማክሰኞ፣ በችሎቱ የሁለተኛ ቀን ውሎ ከሕዝብ ከተውጣጡት እና የመመረጥ ዕድል ከገጠማቸው ለዳኝነት ሊቀመጡ ከሚችሉት ግለሰቦች የተወሰኑትን አሰናበቱ።
በደንቡ መሰረት ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው በብቃት መዳኝነት ይችሉ እንደሆን ማጣሪያ በሚደረግበት ሂደት ወቅት ከቀረቡት ሰዎች ውስጥ አንዲት የኒው ዮርክ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሴት ለሊቱን ስለጉዳዩ ሲያስቡ ‘ገለልተኛ እና አድሏዊ ሳይሆኑ መፍረድ እንደማይችሉ’ መገንዘባቸውን ጉዳዩን ለሚያስችሉት የግዛቲቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሁዋን መርቻን ተናግረዋል። አንድ ሌላ ግለሰብም፣ “ተስፋ የማደርገውን ያህል ገለልተኛ እና ከአድሎ ነጻ መሆን የምችል አይመስለኝም” ሲሉ ያደረባቸውን ሥጋት ለፍርድ ቤቱ ገልጠዋል። ከሪፐብሊካን ፓርቲ ወገን የሆኑ በርካታ ወዳጆች እና ዘመዶች እንዳሏቸው ያመለከቱ አንድ ሌላ ግለሰብ ደግሞ፡ ‘በዚህ የተነሳ ሳይታወቀኝ ለእነርሱ ላደላ እችል ይሆናል’ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸው በተመሳሳይ ከዳኝነቱ ዕጣ ተሰናብተዋል።
በሚቀጥለው ዓመት በጥቅምት ወር መገባደጃ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲያቸው እጩ በመሆን ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋራ የሚፎካከሩት ትራምፕ፣ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2016 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸንፈው ወደ ዋይት ሃውስ ከመግባታቸው አስቀድሞ ‘ከጋብቻ ውጪ የሆነ ግንኙነት ፈጽመዋል’ በሚል የተነሳውን ጉዳይ ለመሽፋፈን ‘በከፈሉት ገንዘብ እና ሚስጥር ለመደበቅ በማሴር’ በሚል ነው የተከሰሱት።
መድረክ / ፎረም