የኒጀር ወታደራዊ አገዛዝ ሀገሪቱ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን የጦር ውል በማቋረጥ የሩሲያ ጦር አሰልጣኞችን በተቀበለ ማግስት ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች የአሜሪካ ወታደሮች ከሀገሪቱ እንዲወጡ የሚጠይቅ ሰልፍ በመዲናዋ አድርገዋል።
በማዕከላዊ ኒያሚ ክንድ እና ክንድ ተቆላልፈው፣ የኒጀር ሰንደቅ ዓላማን እያውለበለቡ ዜጎች ያደረጉት ሰልፍ ፣ ባለፈው ዓመት ወታደራዊ ኃይሉ ስልጣን በመፈንቅለ መንግስጥ ከተቋናጠጠ በኃላ የፈረንሳይ ጦር ከኒጀር እንዲወጣ የገፋውን ጸረ ፈረንሳይ ሰልፍ አስታዋሽ ሆኗል።
መፈንቅለ መንግስቱ ከመደረጉ በፊት ፣ ኒጀር አስርት ዓመታትን ያስቆጠረውን ምዕራብ አፍሪካ የእስላማዊ ኃይሎች ጥቃት ለመመከት ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ስቴትስ የጦር መንደራቸውን የተከሉባት ቁልፍ የጸጥታ አጋር ነበረች።
ይሁና አሁን ላይ ፣ የጎረቤት ሀገራቱ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ የጦር አገዛዞች ጎራ የተቀላቀለችው ኒጀር አዳዲስ ባለስልጣናት ፣ ከምዕራቡ ዓለም አጋሮች ጋር የተደረጉ የጦር ስምምነቶችን ቋጭተዋል ፣ ከቀጠናው የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተቋም ኢኮዋስ በመውጣት ከሩሲያ ጋር ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል።
ረቡ ዕለት የሩሲያ ጦር አሰልጣኖች እና መሳሪያዎች ኒጀር መድረስ ፣ የጁንታው አስተዳደር አፍሪካ ውስጥ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማጎልበት ከምትሻው ሞስኮ ጋር የቅርብ ትብብር ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት ያሳያል ተብሏል ።
በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ጥቂት የሩስያ ሰንደቅ ዓላማዎች ታይተዋል ። ይሁና አንዳንድ ዜጎች ለሮይተርስ እንደተናገሩት አቀባባል የተደረገለት የሩሲያ መከላከያ ድጋፍ በኒጀር ውስጥ በቋሚነት ስፍራ እንዲሰጠው አይፈልጉም።
ሱሊማኒ ኦስማኒ የተባለ አንድ ተማሪ ፣" ፈረንሳይ ፣ አሜሪካም ሆነ ሌሎች ሀገራት በዚህ መንገድ ነበር ኒጀር ውስጥ የተቀመጡት ። ከጦር ትብብር ተነስተው ፣ የሀገራችንን ሰፊ ክፍል ይቆጣጠራሉ " ብሏል ።
የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ኒጀርን ለቀው ይወጡ እንደሆን ፣ ከወጡም መቼ እንደሚወጡ እስካሁን ግልጽ አይደለም ።
መድረክ / ፎረም