በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ወርሃ መጋቢት በታሪክ በዓለም ሞቃታማው ወር ሆኖ አለፈ


 ከሲም ፓራጎን የገበያ አዳራሽ ባንኮክ ሙቀት ለመቋቋም ዣንጥላ ዘርግተዋል፡፡
ከሲም ፓራጎን የገበያ አዳራሽ ባንኮክ ሙቀት ለመቋቋም ዣንጥላ ዘርግተዋል፡፡

በየወሩ አዲስ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በተከታታይ ከተመዘገበባቸው ያለፉት 10 ወራት ውስጥ፣ ከቀናት በፊት የተገባደደው የአውሮፓውያኑ የመጋቢት ወር፣ በዓለም ታሪክ ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት ወር ሆኖ ማለፉን ‘የአውሮፓ ሕብረት የአየር ንብረት ለውጥ ክትትል አገልግሎት’ የተባለው ተቋም በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

በአጽህሮት ሶስት C እና S በመባል የሚታወቀው፡ የአውሮፓ ሕብረቱ ኮፐርኒከስ የአየር ንብረት ለውጥ መከታተያ ፕሮግራም፣ በወርሃዊ መጽሔቱ እንዳስታወቀው፤ ያለፉት 10 ወራት እያንዳንዳቸው እጅግ ሞቃታማ ወራት ሆነው ሲመዘገቡ፤ በመጋቢት ወር ያበቁት 12 ወራትም በጠቅላላው በምድሪቱ ከተመዘገቡት እጅግ ሞቃታማ 12 ወራት ውስጥ መመደባቸውን አመልክቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሚያዝያ 2023 እስካለፈው መጋቢት 2024 ድረስ የታየው የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን፣ በ1850 እና በ1900 መካከል ባሉት ዓመታት ከነበረው በ1 ነጥብ58 ዲግሪ ሴልሲየስ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁሟል። የፕሮግራሙ ምክትል ዲሬክተር ሳማንታ በርጌስ ትላንት ሰኞ ለሮይተርስ በሰጡት ቃል፣ “እጅግ የተለየ ሁኔታ እየታየ ያለበት ይህ አዝማሚያ፣ ከረዥም ጊዜ አንድምታው አንጻር በጣም ያሳስበኛል” ብለዋል። በርጌስ አክለውም እንዲህ ያሉ የተጋነኑ አዝማሚያዎችን “በየወሩ ማየት፤ የአየር ንብረታችን ይዞታ እየተቀየረ ብቻ ሳይሆን፣ በፍጥነት እየተቀየረ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።

ተመራማሪዎች፣ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1940ዎቹ አንስቶ ከተሰበሰቡ የቀደሙ መረጃዎች በማነጻጸር የተመለከቱት ያለፈው ወር ሪኮርድ፣ ‘ቅድመ-ኢንዱስትሪ’ ከተባለው ጊዜ አንስቶ እጅግ ሞቃታማው ወር መሆኑን አረጋግጠዋል። ሙሉ ዓመቱ 2023’ም ከ1850’ዎቹ ወዲህ ምድሪቱ ከፍተኛ ሙቀት ያስመዘገበችበት ሆኖ አልፏል።

በተዛመደ ሌላ ዜና፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በአማዞን ደን አካባቢ የተከሰተ ድርቅ፣ ከጥር እስከ መጋቢት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ በቬንዝዌላ ካሁን ቀደም ታይቶ የማያውቅ ብዛት ያለው የሰደድ እሳት እንዲቀሰስ ምክንያት ሲሆን፤ በደቡባዊ አፍሪቃ የተከሰተው ድርቅ ደግሞ በእርሻ ማሳዎች ላይ የነበረውን ሰብል ሙሉ በሙሉ በማውደም ሚሊዮኖችን ለረሃብ መዳረጉ ተዘግቧል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG