በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፖላንድ የአየር ግዛቴን ጥሳብኛለች ካለቻት ሩሲያ ማብራሪያ ጠይቀች



ምስሉ በሞስኮ በሚገኘው የክሬምሊን ምክር ቤት ህንፃ ጉልላት ላይ የሩስያ ሰንደቅ ሲውለበለብ ያሳያል ።
ምስሉ በሞስኮ በሚገኘው የክሬምሊን ምክር ቤት ህንፃ ጉልላት ላይ የሩስያ ሰንደቅ ሲውለበለብ ያሳያል ።

ፖላንድ ተፈጽሞብኛል ያላችውን አዲስ የአየር ክልል ጥሰት በተመለከተ ከሩሲያ ማብራሪያ እንደምትጠይቅ አስታወቀች ።
እሁድ ማለዳ ወደ ዩክሬን ከማቅናቱ በፊት የሩሲያ ሚሳኤል የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አባል ሀገሯን ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል የአየር ግዛት መጣሱን የፖላንድ ጦር ቃል አቀባይ ተናግረዋል ።

"የፖላንድ የአየር ክልል በሩሲያ የአየር ኃይል በተተኮሰ ክሩዝ ሚሳዬል ተጥሷል '' ፣ በማለት በኤክስ ማህበራዊ አውታር ላይ ያተመው የፖላንድ ጦር ፣ ተተኳሹ በሉቢን ግዛት -ኦሰርዶ መንደር ላይ 39 ያህል ሴኮንዶች እንደቆየም አክሏል ።

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፓውል ሮንስኪ በበኩላቸው ፣ " ከሁሉም በላይ ፣ የሩሲያ ፌዴሬሽንን በዩክሬን ህዝብ እና ግዛት ላይ የሚያደርገውን የሽብር አየር ጥቃት እንዲያቆም ፣ ጦርነቱን በመግታት በራሱ የውስጥ ችግሮች ላይ እንዲያተኩር እንጠይቃለን " ብለዋል ፣ ለሮይተርስ የዜና አውታር ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ፣ ሩሲያ ባለፉት አራት ቀናት ለሶስተኛ ጊዜ የሚሳኤል ጥቃት እንደፈጸመችባት አስታውቃለች ። ኪየቭ ከተማ ላይ ያነጣጠረ ሁለተኛው ጥቃት መሆኑ ነው ። አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው በኪዬቭ የአየር ማስጠንቀቂያ ደወል ከሁለት ሰዓታት በላይ ተሰምቷል ።

ሩሲያ በክራይሚያ ሴባስቶፖል 10 የዩክሬን ሚሳኤሎችን እንደመታች እና በባክሙት አቅራቢያ ያለች መንደር መያዟን የሩሲያ ባለስልጣናት ቅዳሜ ዕለት አስታውቀዋል ።

ዩክሬን በመሳሪያ እጥረት በተፈተነችበት በአሁኑ ወቅት ፣ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚገኙ በርካታ መንደሮችን ተቆጣጥራለች።

ቅዳሜ ዕለት የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የኢቫኒቪስኬን መንደር እንደተቆጣጠ ተናግሯል ። የቻሲቭ ያር ከተማ በቅርብ የሚገኝ ሲሆን ከዚያ ተሻግሮ የክራማቶርስክ ከተማ ይገኛል ።

የምድር ጦርነቱ ያዘገመ ቢሆንም ፣ ሁለቱ የጦር ኃይሎች የአየር ጥቃቶችን ቀጥለዋል ።

ሩሲያ በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ አርብ ዕለት ካደረሰችው ግዙፍ ጥቃት በማገገም ላይ የምትገኘው ዩክሬን ፣ ከ34 ከጥቃት አድራሽ ሰው አልባ ጠያራዎች (ድሮኖች) 31 ያህሉን በመምታት መጣሏን የሀገሪቱ የጦር ኃይል ቅዳሜ ዕለት አስታውቀዋል (ቪኦኤ)።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG