በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በጋዛ ከተማ ሆስፒታል ላይ የጥቃት ዘመቻ ጀመረች


በደቡብ እስራኤል የታየው ጭስ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 17/2024 ዓ.ም
በደቡብ እስራኤል የታየው ጭስ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 17/2024 ዓ.ም

የእስራኤል ጦር ጋዛ ከተማ በሚገኘው ሺፋ ሆስፒታል ላይ የጥቃት ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ሰኞ ዕለት አስታውቋል። ጦሩ በኅዳር ወር በአካሄደው ተመሳሳይ ወረራ ትችት ደርሶበት ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሀጋሪ ባወጡት መግለጫ፣ "የእስራኤል ጦር ሰኞ ዕለት ጥቃቱን ማካሄድ የጀመረው የሐማስ ባለሥልጣናት ሆስፒታሉን በእስራኤል ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለማዘዝ እየተጠቀሙበት በመሆኑ ነው" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አክለው "ይህን ዘመቻ የምናካሂደው በጥንቃቄ እና ሆስፒታሉ አስፈላጊ ሥራውን መቀጠል በሚችልበት መልኩ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

በጋዛ ሰርጥ ትልቁ በሆነው ሆስፒታል አካባቢ የአየር ድብደባ እየተካሄደ መሆኑን እና የእስራኤል ታንኮችም ሲንቀሳቀሱ መታየታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና እስራኤል በጋዛ "ረሃብ እያስነሳች ነው" ሲሉ ሰኞ ዕለት በብራስልስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተናገሩት የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል፣ ረሃብን "እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመች ነው" ሲሉም ከሰዋል።

ቦሬል አክለው "ጋዛ ረሃብ አፋፍ ላይ አይደለም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እየጎዳ ያለ ረሃብ ውስጥ ናቸው" ብለዋል።

የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ መንግሥታቸውን መርዳት የሚፈልግ ማንኛውም አካል በምድር፣ በአየር እና በባህር ሰፊ ሰብአዊ ርዳታ ወደ ጋዛ እንዲያስገባ ይፈቅዳል ቢሉም፣ ሰብአዊ ተቋማት ግን ወደ ጋዛ ርዳታ እንዳያጓጉዙ በእስራኤል እንደሚታገዱ እና በቀጠለ ግጭት ምክንያት ወደ ጋዛ መግባት አለመቻላቸውን በተደጋጋሚ ይገልፃሉ።

ጦርነቱን እንዲያቆሙ የሚደረግባቸውን ዓለም አቀፍ ጫና እሁድ ዕለት ውድቅ ያደረጉት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው፣ እስራኤል በራፋህ በሚገኙ የሐማስ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ማካሄዷን ትቀጥላለች ብለዋል።

"የትኛውም ዓለም አቀፍ ጫና የጦርነቱን ዓላማ ከማሳካት አያቆመንም" ሲሉ ለካቢኔያቸው በቪዲዮ የተቀረፀ መልዕክት ያስተላለፉት ኔታንያሁ፣ "ያንን ለማድረግ በራፋህም ዘመቻ እናካሂዳለን" ብለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG