የመንግስታቱ ድርጅት ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚዎች በአስጊ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን አስከፊ የሆነ ርሃብ ለመታደግ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እንዲያመቻቹ ትላንት አርብ ጠየቀ።
አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀረው የሱዳኑ ጦርነት አምስት ሚሊየን ሱዳናዊያን አስከፊ የሆነ የምግብ ዋስትና ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ከመንግስታቱ ድርጅት ሰነድ ላይ ማረጋገጥ መቻሉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና አውታር አረጋግጧል።
በጦርነቱ በጠቅላላው ለርሃብ አደጋ የተጋለጡት ሱዳናዊያን 18 ሚሊየን የሚደርሱ ሲሆን 5 ሚሊየኑ አስከፊ በሆነ ርሃብ ውስጥ ይገኛሉም ተብሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ዋና ሃላፊ ማርቲን ግሪፍዝ ለጸጥታው ምክርቤት በጻፉት ደብዳቤ በቀጣዮቹ ወራት “5 ሚልየን ህዝብ አደገኛ ወደ ሚባል ርሃብ እና ጠኔ ይሸጋገራል” ብለዋል። በተጨማሪም ግሪፍዝ 240 ሺህ የሚሆትን በዳርፉር ያሉ ህጻናትን ጨምሮ በድምሩ 730 ሺህ ሱዳናዊያን ህጻናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው ብለዋል።
ግሪፍዝ “አሁን እውነታው የሚገልጥበት ሰዓት ነው። በሱዳን በውጊያ ላይ የሚገኙት አካላት የሲቪሎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረስ ማድረግ አለባቸው” በማለት በኤክስ ማኅበራዊ አውታር ላይ አስፍረዋል። የመንግስታቱ ድርጅት በሱዳን ድጋፍ ለማድረግ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚሻ አስታውቋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ አሌሳንድራ ቬሉቺ በሱዳን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረስ 2.7 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ የገለጹ ሲሆን ነገር ግን ከዚህ ገንዘብ መስብሰብ የተቻለው አምስት በመቶ ብቻ እንደሆነም በጄኔቫ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም