በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኔቶ ዋና ጽህፈት ቤት ለስዊድን አቀባበል ተደረገ


የስዊድን ኔቶን መቀላቀል አስመልክቶ በስቶኮልም በተካሄደው ሥነ-ስርዓት፣ የኔቶ ሰንደቅ አላማ ከስዊድን ሰንደቅ አላማ አጠገብ ሲውለበለብ ታይቷል
የስዊድን ኔቶን መቀላቀል አስመልክቶ በስቶኮልም በተካሄደው ሥነ-ስርዓት፣ የኔቶ ሰንደቅ አላማ ከስዊድን ሰንደቅ አላማ አጠገብ ሲውለበለብ ታይቷል

የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አገሮች ድርጅት (ኔቶ) ብራሰልስ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ሰኞ ለስዊድን ኦፊሴላዊ አቀባበል አድርጎላታል፡፡ የቃል ኪዳን ድርጅቱ 32ኛ አባል የሆነችው የስዊድን ሰንደቅ ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ በ በቃል ኪዳን ድርጅቱ ዋና ጽህፈት ቤት ከተሰቀለ በኋላ የአቀባበል ሥነ ስርዓቱ ተከናውኗል፡፡

ሥነ ስርዓቱን ተከትሎ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የስዊድን ጠቅላይ ሚንስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን ከኔቶ ዋና ጸኃፊ ዬንስ ስቶልተንበርግ ጋር ሆነው ኔቶ ይበልጡን እየተጠናከረ እና አንድነቱም እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

“ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የጸጥታው ሁኔታ በዚህ ደረጃ የከፋበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ክሪስተርሰን “ ሩሲያ ለዩሮ አትላንቲክ ቀጣና ደህንነት ስጋት መደቀኗ ይቀጥላል፡፡ ስዊድንም ኔቶን ለመቀላቀል የጠየቀችው የራሷ ደህንነት እንዲጠበቅ ብሎም የሌሎችንም ደህንነት ለመጠበቅ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሩሲያ እ.አ.አ በ2022 ዓም ዩክሬይንን መውረሯ ለዓመታት ገለልተኛ ወታደራዊ ቁመና ይዘው የኖሩት ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል እንዲፈልጉ አድርጓል፡፡ የሩስያ ፕሬዚደንት ቪላዲሚር ፑቲን ዩክሬይንን በመውረራቸው መዘዝ አምጥቶባቸዋል” ሲሉ የኔቶ ዋና ጸኃፊው ተናግረዋል፡፡

“ፑቲን እንዳያድግ እሳቸው ጎረቤቶቻቸውን በይበልጥ እንዲቆጣጠሩ ፈልገው ነበር፡፡ ሉዓላዊቱን ዩክሬይንን ሊያፈርሷት ሞከሩ አልተሳካላቸውም፡፡ ነገር ግን ኔቶ አድጓል፡ ተጠናክሯል፡፡ ዩክሬይንም ከምንጊዜውም ይበልጥ የህብረቱ አባል ለመሆን ተቃርባለች” ሲሉ ስቶልተንበረግ አክለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ስዊድንን በኔቶ አባልነት በይፋ አቀባበል ያደረጉላት ሲሆን ባለፈው ሳምንት ወደ 20 ሺህ የሚሆኑ የስዊድን የጦር ሠራዊት አባላት ፊንላንድ እና ኖርዌይ ውስጥ ከሁለቱ ሀገሮች ወታደሮች ጋር በኔቶ ወታደራዊ ልምምድ ተሳትፈዋል፡፡

ቱርክ ከበርካታ ወራት እምቢታ በኋላ በያዝነው እ.አ.አ 2024 ዓም መጀመሪያ ላይ ስዊድን አባል እንድትሆን መፍቀዷ ሲታወስ ሀንጋሪም በቅርቡ ይሁንታዋን ሰጥታለች፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG