በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ በሦስት ግዛቶቼ የአየር ክልል ላይ የዩክሬይንን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥያለሁ ስትል አስታወቀች


በዶኔክስ ክልል አቃቤ ህግ ቢሮ ይፋ የተደረገው ይህ ፎቶ፣ የሚሳይል ጥቃቱን ተከትሎ የወደሙ መኪናዎችን እና የተጎዱ መኖሪያ ቤቶች ያሳያል።
በዶኔክስ ክልል አቃቤ ህግ ቢሮ ይፋ የተደረገው ይህ ፎቶ፣ የሚሳይል ጥቃቱን ተከትሎ የወደሙ መኪናዎችን እና የተጎዱ መኖሪያ ቤቶች ያሳያል።

የሩስያ የጦር ኃይል ዩክሬይን በግዛታችን ላይ በሰው አልባ አእውሮፕላኖች የሰነዘረቻቸውን ጥቃቶች አክሽፈናል ሲል አስታወቀ፡፡

ብሪያንስክ፡ ኦሪዮል እና ቤልጎሮድ ግዛቶች ውስጥ በእያንዳንዳቸው ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትተን ጥለናል ሲል የሩስያ የመከላከያ ሚንስቴር አስታውቋል፡፡

የዩክሬይን የመከላከያ ሚንስቴር በበኩሉ ሩስያ ዶኔትስክ፡ ሱሚ፡ ድኒፕሮፔትሮቭስክ እና ካርኪቭ ክፍለ ግዛቶቻችን ላይ የአየር ጥቃት ልታደርስ አቅዳለች ሲል ዛሬ ሰኞ አስጠንቅቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬይን ከሁለት ዓመታት በፊት ወረራ ከከፈተችባት ከሩስያ ጋር “ለመደራደር መቁረጥ አለባት” የሚል አስተያየት የሰጡትን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በተዘዋዋሪ ነቅፈዋቸዋል፡፡

ትናንት ዕሁድ በሳምንታዊው ንግግራቸው “ለሰው ሕይወት እና ለሰብዓዊነት የቆማችሁ፣ በጸሎት በውይይት እና በተግባር እየረዳችሁ ናችሁ“ ብለው ያመሰገኑት ዜሌንስኪ አስከትለውም “ ቤተ ክርስቲያን ማለት እንደዚህ ከሕዝብ ጎን የሚቆም እንጂ 2500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ “ልኑር የሚለውን ሊገድሉት ከሚፈልጉት ጋር በቪዲዮ ለመሸምገል የሚፈልግ አይደለም” በማለት አቡነ ፍራንሲስ ለስዊስ የዜና ማሰራጫ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የተናገሩትን በተዘዋዋሪ ጠቅሰዋል፡፡

የዩክሬይን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚትሮ ኩሌይባም የአቡኑን አስተያየት ነቅፈው በማሕበራዊ መገናኛ ባወጡት ጽሁፍ “ ለቢጫ እና ሰማያዊ ሰንደቅ ዓላማችን እንኖራለን፣ እንሞታለን፣ ድል እናደርጋለን እንጂ እጅ ሰጥተን የማንንም ባንዲራ አንሰቅልም” ብለዋል። አቡነ ፍራንሲስን አስመልክተው “ ተቃራኒዎቹን ወገኖች እኩል አድርገው በመመልከት ድርድር አይበሉ፣ ይልቁንም ከትክክለኛው ወገን ጋር ይቁሙ“ ብለዋቸዋል፡፡

የቫቲካን ቃል አቀባይ ማቴዎ ብሩኒ ለትችቶቹ በሰጡት ምላሽ “ አቡነ ፍራንሲስ ውጊያውን ለማቆም እና ለመደራደር ቁርጠኞች ሁኑ አሉ እንጂ ዩክሬይን እጅ ትስጥ አላሉም” ብለዋል፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በቅርቡ ከስዊስ የዜና ማሰራጫ RSI ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ዩክሬይን ከሩስያ ጋር የሰላም ድርድር ማድረግ አለባት በሚሉ ወገኖች እና ከተደራደረች የሩስያን ወረራ ትክክለኛ ቁመና ይሰጣል በሚሉ ወገኖች መካከል ስላለው ክርክር ተጠይቀው ነበር። "እንደኔ አስተያየት፣ ጎበዙ ሁኔታውን ገምግሞ፣ ህዝቡን አስቦ፣ ነጩን ባንዲራ አውለብልቦ የሚደራደረው ነው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

ካርዲናል ቲመቲ ዶናልም በሰንበት ስብከታቸው የአቡኑን አስተያየት ካሉበት አግባብ ውጭ መተርጎም አይገባም ሲሉ አሳስበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG