በሱዳን የረመዳን ተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት አርብ እለት ባሳለፈው ውሳኔ ጠይቋል። የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ በዚህ ሳምንት ባደረጉት ንግግርም፣ በሱዳን ያለው ቀውስ "እጅግ በጣም ከፍተኛ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የውሳኔ ሃሳቡን ያረቀቁት የእንግሊዝ ምክትል አምባሳደር ጄምስ ካሪኡኪ፣ "የፀጥታው ምክርቤት በዚህ የውሳኔ ሃሳብ፣ የሱዳን ጦር ኃይሎች እና ፈጥኖ ደራሹ ኃይል፣ በረመዳን ፆም ወቅት አስቸኳይ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲያደርጉ ጠንከር ያለ እና ግልፅ መልዕክት አስተላልፏል" ብለዋል።
የሙስሊሞች ቅዱሱ ረመዳን ፆም በመጪው ሳምንት የሚጀምር ሲሆን ለአንድ ወር ይቆያል።
ካሪኡኪ አክለው "የውሳኔ ሃሳቡ የተላለፈው፣ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ እና የአፍሪካ ህብረት ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ነው" ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ሮበርት ዉድ በበኩላቸው፣ አንድ አመት ሊሞላው ጥቂት ጊዜ በቀረው ጦርነት፣ በውጊያው ተሳታፊ የሆኑ ሁለቱም ወገኖች የፈፀሟቸውን አሰቃቂ ድርጊቶች አውግዘው "ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። ይህን ግጭት የሚያባብሱትን የጦር መሳሪያ አቅርቦቶች ለመከላከል እና ለማስቆም ተባብረን መስራት አለብን" ብለዋል።
የፀጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሃሳቡን በአብላጫ ድምፅ ያፀደቀው ያለምንም ተቃውሞ እና በሩሲያ ድምፀ ታእቅቦ ነው።
መድረክ / ፎረም