ጋዛን በተመለከተ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ እንዲሁም የታገቱ ሰዎች እንዲለቀቁ ለማስቻል የሚደረጉ ድርድሮች በግብጽ እና ካታር አደራዳሪዎች በኩል በዛሬው ዕለት ካይሮ ውስጥ ቀጥለዋል። በአዲሱ የድርድር ማዕቀፍ ዙሪያ ከሐማስ ምላሽ እንደሚጠበቅ ዘገባዎች አመላክተዋል።
እስራኤል ከሞላ ጎደል ማዕቀፉን እንደተቀበለች አንድ ከፍተኛ የፕሬዚደንት ባይደን አስተዳደር ባለስልጣን ቅዳሜ ዕለት አስታውቀዋል።
"በአሁኑ ሰዓት ፣ ኳሷ በሐማስ ክልል ውስጥ ትገኛለች ። በምንችለው መጠን ሁሉ አጥብቀን እየገፋን ነው " ፣ ሲሉ በጉዳዩ ላይ በአደባባይ ለመናገር ያልተፈቀደላቸው መሆኑን በመጥቀስ ስማቸው በሚስጢርነት እንዲያዝ የጠየቁት ባለስልጣን ለዘጋቢዎች ተናግረዋል።
በተደራዳሪዎች ዘንድ ቅቡል መሆን የሚጠይቀው ማዕቀፍ ለስድስት ሳምንታት ያህል የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ እና ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ታጋቾች እንዲለቀቁ ይጠይቃል። ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ እንዲገባም ይፈቅዳል።
እኒሁ ባለስልጣን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የተኩስ አቁም ንግግሮቹ ውጤት "ይህ ይሆናል" ብሎ አስቀድሞ መናገር እንደማይሹ አክለው ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ሐማስ ጦርነቱን ሙሉ በሙሉ ለማቆም የሂደቱ መጀመሪያ ጊዜያዊ የተኩስ ተግታ መሆን አለበት ከሚለው አቋሙ ወደ ኋላ እንዳላለ የግብጽ ምንጮች እና የሐማስ ባለስልጣን ተናግረዋል።
አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እሁድ ማለዳ እንደዘገበው አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለስልጣን እስራኤል የሐማስን ጥያቄዎች ከተቀበለች ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ ይቻላል ብለዋል።
አደራዳሪዎች የእስልምና እምነት ተከታዮች የጾም ወር ረመዳን ከመጀመሩ በፊት ተደራዳሪዎች ጊዜያዊ የተኩስ አቁም አፍታ ላይ እንዲደርሱ ሲሰሩ ቆይተዋል ። ለአምስት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ የዘለቀው እና በሐማስ የምትመራው ጋዛን ያወደመው ግጭት እንዲቆምም ተስፋ ሰንቀዋል።
መድረክ / ፎረም