በሃማስ የታገቱ እስራኤላዊያንን ለማስለቀቅ እየተደረገው ባለው ድርድር መካከል በእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ መሪ ዴቪድ ባርኔ የሚመራ ልዑክ በሰላም ዙሪያ ለመወያየት ዛሬ ቅዳሜ ፓሪስ ይገናኛሉ። የሰላም ተደራዳሪዎቹ በጋዛ የተኩስ ልውውጥ እንዲቆም፣ እስራኤል የሚሊዮኖች መጠለያ በሆነው በደቡባዊ ጋዛ ራፋ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ለመቀልበስ እንደሚሰሩ ተገልጿል።
ቅዳሜ እና እሁድ በሚካሄደው ውይይት ዙሪያ እስራኤል በይፋ ያለችው ነገር የለም። የእስራኤል ሃይሎች ከትላንት አርብ አንስቶ በጋዛ ዴይር አል ባላህ፣ ካሃን ዩኒስ እና ራፋ ባሉ የተለያዩ ስፍራዎች ጥቃት ፈጽመዋል። በሃማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በጥቃቱ 92 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሃማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ በካይሮ ከግብጽ ተደራዳሪዎች ጋር ከበባውን በተመለከተ በዚህ ሳምንት የመጀመሪያውን ውይይት አድርገዋል። ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሃማስ ባለስልጣን ሃማስ በግብጽ በነበረው ውይይት ምንም ዓይነት የድርድር ሃሳብ እንዳላቀረበ እና ተደራዳሪዎቹ ይዘው የሚመለሱትን ብቻ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ለካቢኒያቸው ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ የጋዛን የጸጥታ ሁኔታ በተመለክተ ያላቸውን የደህንነት እቅድ አስታውቀዋል። ኔታኒያሁ እስራኤል ሙሉ ለሙሉ ስፍራውን ከሃማስ ካጸዳች በኋላ የጋዛ ሰርጥ በዌስት ባንክ ያለውም የፍልስጤም አመራርም ሆነ በማንም ስር ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ አመራሩ እና የደህንነት ቁጥጥሩ በእስራኤል ስር እንደሚሆን አስታውቀዋል። እቅዱ የግብጽን እና የዩናይትድ ስቴትስን ትብብር የሚሻም ነው። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ እቅዱ የግብጽ ይሁንታን ማግኘቱ አልተረጋገጠም። የዩናይትድ ስቴትስ ኬብል የዜና ጣቢያ ሲኤንኤን፤ ግብጽ እቅዱን በተመለከተ በቦታው የፍልስጤም አመራር እንዲኖር የምትሻውን የዩናይትድ ስቴትስን አቋም ልትጋራ እንደምትችል ዘግቧል።
እቅዱ ዋሽንግተን በስፍራው እንዲኖር የምትሻው የሁለት ሀገሮች መንግስት መፍትሄ በተጻራሪ የቆመም ነው። እቅዱን የተመለከቱ የፍልስጤም ተወካዮች ሙሉ ለሙሉ መቃወማቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ሀማስ እስካሁን ድረስ 100 የሚሆኑ የእስራኤል ታጋቾችን እንደያዘ ይገኛል። ሀማስ እስራኤል ከጋዛ ከበባዋን ለቃ ከወጣች ታጋቾቹን ሙሉ ለሙሉ እንደሚለቅ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ኔታኒያሁ የሀማስን እቅድ “ቅዠት” ሲሉ አጣጥለውታል።
መድረክ / ፎረም