የማላዊ ፕሬዘዳንት ላዛረስ ቻክዋሬ የማላዊ ኢሚግሬሽን ቢሮ በደረሰበት የሳይበር ጥቃት ምክንያት ፓስፖርት መስጠት ማቆሙን አስታወቁ። ፕሬዘዳንቱ ረቡዕ ዕለት በፓርላማ ፊት ቀርበው ሀገሪቱ የደረሰባት የሳይበር ጥቃት ደህነቷን አደጋ ላይ የጣለ ነው በመሆኑንም ይሄንን ለመከላከል እየጣርን ነው ያሉ ሲሆን፤ ጥቃት አድራሾቹ ሚሊዮን ዶላሮችን እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም መንግስታችን ግን ክፍያውን አይፈጽምም ብለዋል።
በዚህ የተነሳም በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት የሀገሪቱ ኢሚግሬሽን ቢሮ ፓስፖርት አይሰጥም ብለዋል። ማላዊ በጎርጎሮሳዊያን 2021 ቴክኖ ብሬን ከሚሰኘው እና ከዚህ ቀደም ፓስፖርት የማዘጋጀት ውለታ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ገብቶ ከነበረው ተቋም፤ ጋር ውለታዋን ካቋረጠች በኋላ የተደራረቡ የፓስፖርት ጥያቄዎችን ማስተናገድ አቅቷት ቆይታለች። በቅርቡም ከቴክኖ ብሬን ጋር የተወሰኑ የፓስፖርት ጉዳዮችን ለመፈጸም በድጋሚ የተገደበ ውለታ ስትስራ መቆየቷ ይታወቃል።
በማላዊ የዴሞክራሲ እና የምጣኔ ሀብት ልማቶች ተነሳሽነት ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር የሆኑት ሲልቨስትር ናሚዋ ፕሬዘዳንቱ ጥቃቱ እንዴት እና በማን እንደተፈጸመ እንዲሁም የገንዘብ ጥያቄው በምን መልኩ እንደደርሳቸው አለማስታወቃቸውን ተችተዋል። ናሚዋ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን እና በተለያዩ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የቀድሞ አገልግሎት ሰጭ ቴክኖ ብሬን ተጠርጣሪ ሆኗል ያሉ ሲሆን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ቴክኖ ብሬን የተሰኘው ተቋም የመረጃ ስርዓቱን መልሶ ለመልቀቅ ገንዘብ እንዲሰጠው ጠይቋል በማለት እየዘገቡ ይገኛሉ።
ነገር ግን ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ እና በማላዊ የኢሚግሬሽን ተቋም ውስጥ የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ባለሞያዎች ለኢሚግሬሽኑ ማንም የገንዘብ ጥያቄ አለማቅረቡን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል። የማላዊ የኢሚግሬሽን ቃል አቀባይ ዌሊንግተን ቺፖንዴ በአሜሪካ ድምጽ በስልክ ጥሪ እና በቴክስት ለተደረገላቸው የቃለመጠይቅ ግብዣ ምላሽ አልሰጡም፡፡
መድረክ / ፎረም