በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ አልጄሪያ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ የምታቀርበውን እቅድ ውድቅ ታደርጋለች


እስራኤል የካቲት 18፣ 2024፣ በደቡብ ጋዛ የፈፀመችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ፣ ፍልስጤማውያን በራፋ የደረሰውን ውድመት ሲመለከቱ
እስራኤል የካቲት 18፣ 2024፣ በደቡብ ጋዛ የፈፀመችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ፣ ፍልስጤማውያን በራፋ የደረሰውን ውድመት ሲመለከቱ

አልጄሪያ በጋዛ የሚካሄደው የእስራኤል ጦርነት በአፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲቆም የሚጠይቀውን እና በዚህ ሳምንት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለማቅረብ ያሰበችውን እቅድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ እንደምታስቆመው፣ በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር አስታወቁ።

አምባሳደሯ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ትላንት ባወጡት መግለጫ፣ አሜሪካ ለጋዛ ግጭት "ዘላቂ መፍትሄ" ለማምጣት ለወራት ስትሰራ ቆይታለች ያሉ ሲሆን፣ እቅዱ ቢያንስ ለስድስት ሳምንታት በጋዛ አፋጣኝ እና ቀጣይነት ያለው መረጋጋት የሚያመጣ እና፣ የበለጠ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚያስችል እርምጃዎች ለመውሰድ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከእስራኤል፣ ከግብፅ እና ከሌሎችም አገራት በተገኘ ግብዓት እየሰራችበት ያለ እቅድ መሆኑን አመልክተውም፣ "ታጋቾችን በሙሉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት እና ውጊያውን ረዘም ላለ ግዜ እንዲቆም የሚያስችል እና ለፍልስጤማውያን ህይወት አድን ምግብ፣ ውሃ፣ ነዳጅ፣ መድሃኒት እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እንዲደርስ ማድረግ የሚችል ነው" ብለዋል።

የአልጄሪያ እቅድ ግን እነዚህን ውጤቶች ማስገኘት አይችልም ያሉት አምባሳደሯ፣ እንደውም "ከነሱ በተቃራኒው እንደሚሰራ" በመግለፅ፣ የአልጄሪያ እቅድ ለድምፅ የሚቀርብ ከሆነ "አይፀድቅም" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ቅዳሜ እለት በመካከለኛው ጋዛ ባካሄደችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 68 ሰዎች መገደላቸውን፣ የአል-አልቃሳ ሆስፒታል ሰራተኞች ለሲኤን ኤን ተናግረዋል።

የጋዛ ጤና ሚኒስትር እሁድ እለት ባወጣው መግለጫ፣ ከጥቅምት ሰባት ወዲህ ወደ 29 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እና ከ68 ሺህ በላይ መቁሰላቸውን ገልጾ፣ ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህፃናት መሆናቸውን አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG