በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተጀመረ ሶማልያ ኢትዮጵያን ከሰሰች


የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እኤአ የካቲት 17 ቀን 2024 በአዲስ አበባ ከሚካሄደው 37ኛው የአፍሪካ ህብረት ምክር ቤት ስብሰባ በፊት ፎቶ ተነስተዋል። ፎቶ ኤኤፍፒ
የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እኤአ የካቲት 17 ቀን 2024 በአዲስ አበባ ከሚካሄደው 37ኛው የአፍሪካ ህብረት ምክር ቤት ስብሰባ በፊት ፎቶ ተነስተዋል። ፎቶ ኤኤፍፒ

“ኢትዮጵያ ከተገነጠለችው የሶማሌላንድ ክልል ጋር የባህር መዳረሻ ስምምነት በመፈራረም የሀገራቸውን የተወሰነ ክፍል ለመጠቅለል እየጣረች" መሆኑን የሶማልያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ለሁለት ቀናት በሚቆየውና ዛሬ ቅዳሜ በተከፈተው 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተናገሩ፡፡

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው “ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ እኤአ ጥር 1 ቀን የተፈራረሙት ስምምነት፣ የሶማሊያን ክፍል ወደ ኢትዮጵያ ከመጠቅለል እና የሶማሊያን ድንበሮች ከመቀየር ያለፈ ፋይዳ የለውም” ማለታቸውን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ለዚሁ ዓላማ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሶማሌ ላንድ እንደነበሩም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ ወደብ እንዳትገነባ ለማስቆም ሀገራቸው ለጦርነት ዝግጁ መሆንዋን ከዚህ ቀደም የሶማልያው ፕሬዚዳንት መናገራቸው የሚታወስ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ ሶማልያን የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩን ገልጻለች፡፡

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ወር ለምክር ቤቱ በሰጡት መግለጫ ከሶማልያ ጋር ወደ ጦርነት የመሄድ ሀሳቡ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

በ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ መሪዎች ንግግር ያደረጉት ሲሆን የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የአፍሪካ ህብረት ዋና ጸሀፊ ሙሳ ፋኪ መሃመት “መፈንቅለ መንግሥታት እና የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጥሩት ግጭት አህጉሪቱ ወደ ፊት እንዳትሄድ አድርጓታል” ብለዋል፡፡

ሱዳን “እሳት ነበልባል” ውስጥ ናት ያሉት ፋኪ ፣ በሶማሊያ ያለውን የጂሃዲስት ስጋት፣ በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ “የሁልጊዜው ውጥረት”፣ የሳህልን “የሽብር አደጋ” እና በሊቢያ የማያቋርጥ አለመረጋጋት መኖሩን በንግግራቸው በማጉላት ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም "አፍሪካ የጥንታዊ ህዝቦች እና ሥልጣኔ መገኛ ነበረች፤ ለዓለም ሥልጣኔም የድርሻዋን አበርክታለች፤ ነገር ግን በቅኝ ግዛት ወቅት ይህ አቅጣጫውን ቀይሮ፤ በምዕራባውያን ሥልጣኔ ተተክቶ አፍሪካ ሥልጣኔ አልባ ሆናለች" ሲሉ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው ላይ የ49 ሀገራት መሪዎች፣ ከአፍሪካ ውጪ የ6 ሀገራት መሪዎች፣ 13 የዓለም አቀፍ ተቋማት ሀላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

የሞሪታኒያው ፕሬዝዳንት መሐመድ አወልድ ጋዝዋሀኒ ከኮሞሮሱ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሶማኒ ላይ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነትን ተረክበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG