በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቤተክርስቲያን ውስጥ ተኩስ የከፈተች ሴት ተገደለች


ሌክዉድ ቤተክርስትያን ሂዩስተን
ሌክዉድ ቤተክርስትያን ሂዩስተን

በዩናይትድ ስቴትስ ደቡባዊ ግዛት ቴክሳስ ታዋቂው መንፈሳዊ ሰባኪ ጆኤል ኦስቲን በሚሰብኩበት ትልቁ ቤተክርስቲያን ውስጥ ትናንት እሁድ ተኩስ የከፈተች አንዲት ሴት በስፍራው በነበሩ ሁለት ፖሊሶች መገደሏ ተነገረ።

የሂዩስተን ፖሊስ አዛዥ ትሮይ ፊነር ረጅም ሽጉጥ እና ቦርሳ በመያዝ ወደ ሌክዉድ ቤተክርስትያን ገብታለች ያሏት ይቺ ሴት የአምስት ዓመት እድሜ ያለው ህፃን አስከትላ እንደነበር ተናግረዋል።

ሴትየዋ በሥፍራው ስትሞት አብሯት የነበረው ህጻን በነበረው የተኩስ ልውውጥ በጥይት ተመቶ ክፉኛ መቁሰሉን ፖሊስ አስታውቋል።

በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሌላ አንድ ሰው እግሩ ላይ የቆሰለ ቢሆንም በሂዩስተን ሆስፒታል በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል። በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጣ ባለችው ሟችና በተጎዳው ሕፃን መካከል ምን ዓይነት ግኙነት እንዳለ ፖሊስ አልገለፀም። የክስተቱ ምክኒያት ምን እንደኾነም እስካሁን አልተነገረም።

ሰባኪው ጆኤል ኦስቲን “ጉባኤው በተፈጠረው ተኩስ በጣም “ አዝኗል ብለዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው በየሳምንቱ 45,000 ሰዎች በሚታደሙበት ትልቁ ቤተክርስትያን ውስጥ መንፈሳዊ አገልግሎቶች በሚሰጡበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ካሉ ትላልቅ ቤተክርስቲያናት ሦስተኛው ትልቁ ቤተክርስቲያን መሆኑንም ሃርትፎርድ የተባለው የሃይማኖት ምርምር ተቋማ ገልጿል፡፡

በቴሌቪዥን የሚተላለፈው የኦስቲን ስብከት ወደ 100 የሚሆኑ አገሮችንም እንደሚያዳርስ ተመልክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG