የአፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተከናውነዋል። የናይጄሪያ እና ኮትዲዮቫር ብሔራዊ ቡድኖች ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ለፍጻሜው ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። “ኃያል ንስሮች” በሚል ቅጽል የሚታወቀው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ቀደም ባለው የጨዋታ ድልድል መሰረት ከደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ጋር በቡአኪ ስታዲየም ጨዋታውን አድርጓል። ከፍተኛ የመሸናነፍ ትግል በታየበት በዚህ ጨዋታ የናይጄሪያ ቡድን ፣ በ67ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ቀዳሚውን ግብ አስቆጥሯል። ናይጄሪያን ለቀዳሚነት ያበቃት የቡድኑ መሪ የተከላካይ መስመር ተጫዎች ዊሊያም ትሮስት ኢኮንግ ነው።
ግብጻዊው ዳኛ አሚን ሞሀመድ ኦማር መደበኛው ጨዋታ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ናይጄሪያ ያስቆጠረችውን 2ኛ ግብ ቪዲዮ አገዝ ዳኝነትን መሰረት አድርገው ከሻሩ በኃላ ከግቡ ቀደም ብሎ በደቡብ አፍሪካ አጥቂ ላይ የተፈጸመ ጥፋትን አጢነው የፍጹም ቅጣት ምት ዕድል በመስጠት ለ"ባፋና ባፋና"ዎች ያልጠበቁት ሲሳይ አጽድቀውላቸዋል። በ90ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ዕድል ቲቦ ሞኮይና ከመረብ በማገናኘት የደቡብ አፍሪካ ደጋፊዎችን አስደስቷል።
መደበኛው እና ተጨማሪ የጨዋታው ሰዓት በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ ቡድኖቹ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት መለያ ተሸጋግረዋል። የናይጄሪያ ተጨዋቾች ከተሰጣቸው የፍጹም ቅጣት ምት ዕድሎች 4ቱን ለፍሬ ሲያበቁ፣ የደቡብ አፍሪካ ተጫዎቾች በአንጻሩ ሁለት የመለያ ምቶችን በመሳታቸው የናይጄሪያ ቡድን በአጠቃላይ 4-2 ውጤት አሸናፊ ሆኗል።
በመቀጠል በኢቢምፒ ስታዲየም የአዘጋጇ ሀገር ኮትዲዮቫር እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድኖች ተገናኝተዋል ።ከምድቡ በአጠራጣሪ አቋም ወደ ጥሎ ማለፉ ምዕራፍ ያለፈው “ዝሆኖቹ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው የአይቮሪኮስት ቡድን የአሰልጣኝ እና የጨዋታ ስልት ለውጥ ካደረገ በኃላ አዳዲስ ድል ደራርቧል።
የዛሬውም ጨዋታ የቡድኑን ከዕለተ ተዕለት መጠናከር፣ ምናልባትም የዋንጫው ባለቤት ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ሆኖ ተጠናቋል። ስታዲየሙን ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልቶ የሀገሪቱን ብሔራዊ ቡድን ሲያበረታታ ያመሸው በሺዎች የሚቆጠር ደጋፊ ዳግም ጮቤ እንዲረግጥ ያስቻለው ግብ የተቆጠረው በ65ኛው ደቂቃ በሴባስቲያን ሄለር አማካይነት ነው።
የሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ቻምፒዮን ኮትዲዮቫር ቡድን የፊታችን እሁድ ከሶስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል ናይጄሪያ ጋር በኢቢምፒ ስታዲየም ለዋንጫ ይፋለማል። በዋዜማው ደቡብ አፍሪካ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሶስተኛ ደረጃን ለመቆናጠጥ አቢጃን ላይ ይጫወታሉ።
መድረክ / ፎረም