የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ከምንጊዜውም በላይ የተመልካቾችን ቀልብ ሰቅዘው የያዙ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎችን በትናንትናው ዕለት አስተናግዷል።
ቀደም ባለው ሰዓት በ"ቡአኬ" ስታዲየም የተገናኙት አዘጋጇ ሀገር ኮትዲዩቫር እና ማሊ ነበሩ ። በ71ኛው ደቂቃ ኔኔ ዶርግሌስ ከርቀት አክርሮ የመታት ኳስ በኮትዲዮቫር መረብ ላይ በማረፏ ማሊ ጨዋታውን በድል ለመምራት ችላ ነበር ። አንድ ተጫዋቿ ባጠፋው ጥፋት ምክንያት ከሜዳ የተባረረባት ኮትዲዮቫር በ10 ተጫዎቾች አቻ የሚያደርጋትን ግብ ለማስቆጠር የሞት ሽረት ትግል አድርጋለች። ስታዲየሙን በሞላው ደጋፊ ማበረታቻ ዝማሬ እና ጩኸት የተበረታቱ የሚመስሉት የኮትዲዮቫር ተጫዎቾች ልፋታቸው በ90ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል።ሳይመን አዲንጋራ በአስቆጠራት ግብ የቡድኑን ስነ-ልቦና አንሰራርቶ የሀገሩን ኳስ አፍቃሪያን በደስታ አስጨፍሯል።
አሸናፊውን ለመለየት በተጨመሩት 30 ደቂቃዎች ውስጥ ሌላ ታሪክ ተመዝግቧል። ተጨማሪው ሰዓት ተገባዶ ወደ ፍጹም ቅጣት ምዕራፍ ለመሸጋገር 1 ደቂቃ ሲቀር ኦማር ዲያኪቴ በቄንጠኛ ሁኔታ የጨረፋት ኳስ በማሊ መረብ ላይ አልፋለች ። ይቺ ግብ ኮትዲዮቫርን ላልተጠበቀ የድል አፍታ ስታበቃ ፣ የማሊ ቡድን አባላትን ለድንጋጤና እና ብስጭት ዳርጋለች ። ከግቡ በኃላ ከግብጻዊው ዳኛ ሞሀመድ አደል ጋር እሰጥ አገባ ከገጠሙ የማሊ ተጫዎቾች መካከል ሀማሪ ትራወሬ የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል ። በዚህ ጨዋታ ኮትዲዮቫርን ለድል ያበቃትን ግብ ያስቆጠረው ኦማር ዲያኪቴም ከቅጣት አልዳነም። ደስታውን ለመግለጽ መለያ ልብሱን በማውለቁ በተመሳሳይ ከጨዋታው ተውገዷል ። ሀገሩ በሚኖራት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ እንደማይሰለፍ እርግጥ ሆኗል ።
ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል አስገራሚ ስፖርታዊ ክስተቶች የታዩበት ፉክክር በደቡብ አፍሪካ እና በኬፕ ቨርድ መካከል የተደረገ ነበር ። በቻርለስ ኮናን ባኒ ስታዲዮም ያሙሶኩሮ ከተማ ላይ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛ እና ጭማሪ የጨዋታ ደቂቃዎች መሸናነፍ ባለመቻላቸው ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ምዕራፍ ተሸጋግረዋል ። በዚህ ሰዓት ነበር የደቡብ አፍሪካ ግብ ጠባቂ ሮንዊን ዊልያምስ ልዩ ብቃት የታየው ። ሮንዊን ለኬፕ ቨርድ ቡድን ከተሰጡ 5 ፍጹም ቅጣት ምቶች መካከል 4ቱን እየተወረወረ በማዳን ደቡብ አፍሪካ ወደ ግማሽ ፍጻሜ እንድታልፍ ያስቻለ የጨዋታው ጀግና ሆኗል ።
ደቡብ አፍሪካ ለዋንጫ ለማለፍ የፊታችን ረቡ ናይጄሪያን ትገጥማለች ። በዚሁ ቀን በተመሳሳይ አዘጋጇ ሀገር ኮትዲዮቫር ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በኢቤምፒ ስታዲየም ይፋለማሉ ።
መድረክ / ፎረም