ዩናይትድ ስቴትስ በዮርዳኖስ በሚገኘው የጦር ሰፈሯ ላይ ባለፈው እሁድ ለደረሰው ወታደሮቿን የገደለ የሰው አልባ በራሪ "ድሮን" ጥቃት አፀፋ በመካከለኛው ምስራቅ የአየር ጥቃት መፈጸም ጀምራለች።
የሀገሪቱ ማዕከላዊ እዝ ፣ ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ በትናንትናው ዕለት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ እና ተባባሪ ሚሊሻ ቡድኖች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን አስታውቋል ።የዩኤስ ወታደራዊ ኃይሎች ከ85 በላይ ኢላማዎችን የደበደቡ ሲሆን በርካታ የረዥም ርቀት ቦምብ ጣዮችን ያካተቱ አውሮፕላኖች ከዩናይትድ ስቴትስ የበረሩ ስለመሆናቸውም ተገልጿል።
"ለመምታት ያነጣጠርንበትን ሁሉ መታናል። " ሲሉ በመከላከያ ሚኒስትር ውስጥ የአዛዦች ተቋም የስምሪት ኃላፊ የሆኑት ሌዮቴናንት ጄኔራል ዳግላስ ሲምስ ተናግረዋል ። የአየር ጥቃቱ በ30 ደቂቃ ውስጥ የተፈፀመ መሆኑን ገልፀው ከተደበደቡት ስፍራዎች መካከል 3ቱ ኢራቅ ፣ አራቱ ደግሞ ሶሪያ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከአጸፋው ጥቃት በፊት ኢራቅ እንጅ ኢራን እንዳልተጠቀሱ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ተናግረዋል ። የዩኤስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃቶቹ የተፈጸሙት እሳቸው ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
"የእኛ ምላሽ ዛሬ ተጀምሯል ። እኛ በመረጥንባቸው ጊዜያት እና ቦታዎች ይቀጥላል። ዩናይትድ ስቴትስ በመካከለኛው ምስራቅም ሆነ በየትኛውም የዓለም ክፍል ግጭት አትፈልግም። ነገር ግን ሊጎዱን የሚፈልጉ ሁሉ፣ አንድ አሜሪካዊ ቢጎዳ፣ የአጸፋ ምላሽ እንደምንሰጥ ሊያውቁት ይገባል።” ሲሉ ባይደን በአርብ ምሽት መግለጫቸው ላይ አሳስበዋል።
ይሁንና የህዝብ ተወካዮች ምክርት ቤት አፈ ጉባኤው ማይክ ጆንሰን የባይደን አስተዳደር የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ አንድ ሳምንት መዘግየቱን በመጥቀስ ነቀፌታ አሰምተዋል።
ተጨማሪ የአጸፋ ጥቃቶች እንደሚቀጥሉ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም