በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዮርዳኖስ ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች ተገደሉ


ፋይል - ይህ የሳተላይት ምስል፣ ዮርዳኖስ ውስጥ በስተሰሜን ምስራቅ የሚገኘውን እና ታወር 22 በመባል የሚጠራውን የአሜሪካ ጦር ሰፈር ያሳያል - ጥቅምት 12፣ 2023
ፋይል - ይህ የሳተላይት ምስል፣ ዮርዳኖስ ውስጥ በስተሰሜን ምስራቅ የሚገኘውን እና ታወር 22 በመባል የሚጠራውን የአሜሪካ ጦር ሰፈር ያሳያል - ጥቅምት 12፣ 2023

በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገር አንድ ቡድን በዮርዳኖስ በድሮን ባደረሰው ጥቃት፣ ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ፣ በሶሪያ ድንበር አቅራቢያ ደግሞ በደርዘን የሚቆጠሩ መቁሰላቸው ታውቋል።

ወደ ደቡብ ካሮላይና ግዛት በመጓዝ ላይ ለነበሩት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ የብሄራዊ ደህንነት ቡድናቸው ስለ ጥቃቱ የገለፀላቸው ሲሆን፣ በአንድ ቤተክርስቲያን ባደረጉት ንግግር “ምላሽ እንሰጣለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት፣ በአሜሪካ ኃይሎች ላይ ለበርካታ ወራት ድብደባ የተፈፀመ ሲሆን፣ የአሜሪካ ወታደሮችን ሕይወት ሲቀጥፍ ግን ለመጀመሪያ ግዜ ነው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከጥቃቱ ጀርባ ያለውን ቡድን በእርግጠኝነት ለመለየት ምርመራ ማድረጋቸው ሲነገር፣ ባይደንም በትናንቱ ንግግራቸው፣ በኢራን የሚደገፉ ሚሊሺያዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

“ጥቃት ፈፃሚዎቹን በመረጥነው መንገድ ተጠያቂ እናደርጋለን” ብለዋል ባይደን።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለጸው፣ ከዮርዳኖስ በተነሳ ድሮን በደረሰው ጥቃት ቢያንስ 34 ወታደሮች ሲጎዱ፣ ስምንቱ ለሕክምና ከዮርዳኖስ እንዲወጡ ተደርጓል።

ጥቃቱ የደረሰው በዮርዳኖስ፣ ሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር የስንቅ እና ትጥቅ ሠፈር ላይ ሲሆን፣ ለዮርዳኖስ ኃይሎች ምክር እና ድጋፍ የሚሰጡ የአሜሪካ ወታደሮች እንደሚገለገሉበት የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG