በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ዋንጫ "ነብሮቹ"  "ፈርዖኖቹ" ን ድል አደረጉ 


ምስሉ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጫዋቾች ግብ ጠባቂው ሊዮኔል ምፓሲ የማሸነፊያውን ጎል ከአስቆጠረ በኃላ ደስታቸውን ሲገልጹ ያሳያል ።
ምስሉ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጫዋቾች ግብ ጠባቂው ሊዮኔል ምፓሲ የማሸነፊያውን ጎል ከአስቆጠረ በኃላ ደስታቸውን ሲገልጹ ያሳያል ።

ኮትዲዩቫር በመካሄድ ላይ ባለው የአፍሪካ ሀገራት የእግር ዋንጫ ፣ የግብጽ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ የኳስ አፍቃሪያንን ስሜት ሰቅዞ የያዘ የሜዳ ላይ ፍልሚያ በዛሬ ዕለት አድርገዋል።

ከ120 ደቂቃዎች በላይ የተሻገረው የሁለቱ ሀገራት ስፖርታዊ ትግል በፍጹም ቅጣት ምት አሸናፊው ተለይቷል ። በውጤቱም "ነብሮቹ" በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ፣ "ፈርኦኖቹ"ን ድል በማድረግ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል ።

መደበኛው ጨዋታ በተጀመረ በ37ኛው ደቂቃ በሜስቻክ ኤሊያ አማካይነት ቀዳሚውን ግብ ያስቆጠረው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቡድን ቢሆንም የግብጽ ቡድን ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ዕድል ሙስጠፋ ሞሐመድ ወደ ግብ በመቀየር ለጥቂት ደቂቃዎች የቆየውን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ቡድን የበላይነት አምክኖታል። ሀገሩን አቻ አድርጓል ።

አንድ ተጫዎቿን በቀይ ካርድ ያጣችው ግብጽ መደበኛውን እና ተጨማሪውን የጨዋታ ሰዓት በቀሪ 10 ተጨዋቾች ተቋቁማ ለፍጹም ቅጣት ምት ብትደርስም ፣ ለአቻነት ያበቃት ሙስጠፋ ሙሐመድ እና ግብ ጠባቂዋ ሞሃመድ አልሸናዊ ፍጹም ቅጣት ምቶችን በማብለላቸው ምክንያት ከውድድሩ ውጭ ሆናለች ።

ዘንድሮ ላይ አስጋራሚ ብቃት ይዘው ብቅ ካሉ የአፍሪካ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቡድን በበኩሉ አርዘር ማስዋኩ ከሳተው የፍጹም ቅጣት ምት ዕድል ውጭ ያሉትን 8 ምቶች ከመረብ በማዋሀድ የአፍሪካ ዋንጫ የ7 ጊዜ አሸናፊ የግብጽ ብሔራዊ ቡድንን ለመርታት ችሏል ።

በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ታሪክ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቡድን ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ለማሸነፍ ችሏል ። ለመጀመሪያ ጊዜ ለዋንጫ የበቃው በአውሮፓዊያኑ 1968 ዓ.ም ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው 6ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሲሆን ፣ በወቅቱ ቡድኑ የ"ኮንጎ-ኪንሻሳ" ቡድን ተብሎ ይጠራ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ቡድኑ ቻምፒዮን ለመሆን የቻለው በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1974 ዓ.ም ግብጽ ባዘጋጀቸው 9ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው ። በዘመኑ የ"ዛየር" ቡድን በሚል ይታወቅ ነበር ። ለአስርት ዓመታት በተለያዩ ጦርነቶች እና ግጭቶች ስትናጥ የቆየችው ሀገር የቀደመ ታሪኳን የሚያድስ ቡድን ለማፍራት ሳትችል ቆይታለች ።

ቡድኑ የፊታችን አርብ ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገውን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በድል ካጠናቀቀ ከዓመታት በኃላ አዲስ ወርቃማ ታሪክ ለማስመዝገብ ያለው ዕድል በእጅጉ ያላቀ ይሆናል ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG