የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ዕዝ ዛሬ ቅዳሜ ማለዳ ላይ ሠራዊቱ የየመን ሁቲዎች በተያዙት ግዛት ውስጥ “ ቀይ ባህር ላይ ያነጣጠረ እና ለመምታት የተዘጋጀ” ነው ያለውን ፀረ መርከብ ሚሳኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ኮማንድ ቀድሞ ትዊተር በነበረው ኤክስ ገጹ ላይ ሁቲዎቹ በሚቆጣጠሩት ይዞታ ውስጥ የነበረው ሚሳይል ለዩናይትድ ስቴትስ የባህር ሃይል እና የንግድ ምርከቦች ላይ ‘የተጋረጠ አደጋ’ በመሆኑ እርምጃው ተወስዷል ሲል አስታውቋል።
ማርሊን ሉዋንዳ የተባለ የነዳጅ ጫኝ መርከብ አርብ ዕለት አመሻሹ ላይ በተተኮሰ ሚሳኤል ተመትቶ እሳት የተፈጠረ ሲሆን፤ የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪያ አማፅያኑ “በርካታ የባህር ኃይል ሚሳኤሎችን ተጠቅመዋል፣ ጥቃቱ ቀጥተኛ ነበር” ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ወታደራዊ ዕዝ ሴንትኮም የብሪታኒያ የነዳጅ ጫኝ መርከብ የድረሱል ጥሪ ጥሪ ማድረጉን እና ጉዳት እንደደረሰብትም ዘግቧል። የዩናይትድ ስቴትስ ካርኒ መርከብ ከሌሎች መርከቦች ጋር በመጣመር የእርዳታ ምላሽ ሰጥታለች። በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙትን የአሜሪካ ጦር በበላይነት የሚቆጣጠረው ማዕከላዊ ማዘዣ ዕዙ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም ሲል ጨምሮ አስታውቋል።
በተያያዘ ትላንት አርብ የፓናማ ባንዲራ ያለው እና ከህንድ ጋር ግንኙነት ያለው የነዳጅ ምርቶች ጫኝ መርከብ፤ በየመን አቅራቢያ በቀይ ባህር ላይ ሲጓዝ ሁለት ሚሳኤሎች በውሃ ውስጥ ሲፈነዱ መመልከቱን አስታውቋል። በጥቃቱ ምንም ዓይነት የተመዘገበ አደጋ ወይም ጉዳት የለም።
የዓርብ ዕለቱ ጥቃቱ የተፈጸመው ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን የሚደገፉትን በየመን አማፂያን ላይ ያነጣጠረ አዲስ ጥቃት ከጀመሩ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው። ጥቃቶቹ የራዳር ህንጻዎች፣ የሚሳኤል ማስወንጨፊያ ቦታዎች እና፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የመሬት ውስጥ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ስፍራን መምታታቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ጦር አስታውቋል።
ሁቲዎች ከህዳር ወር ጀምሮ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚንቀሳቀሱ የንግድ እና ወታደራዊ መርከቦችን እያጠቁ ነው። ጥቃቱን የከፈቱት ከእስራኤል ጋር ቀጣይነት ባለው ግጭት ውስጥ የሚገኙትን ፍልስጤማውያንን በመደገፍ ነው ይላሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ ሁቲዎች ዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በማስተጓጎል የንግድ እና የተጓዥ መብቶችን እና ነጻነቶችን ጥሰዋል ብሏል።
መድረክ / ፎረም