በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሰሜን ኮሪያ በርካታ ሚሳዬሎችን ወደ ባህር አስወነጨፈች


ፎቶ ፋይል፦ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን
ፎቶ ፋይል፦ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን

ሰሜን ኮሪያ በርካታ የክሩዝ ሚሳዬሎችን በምዕራብ የባህር ዳርቻዋ አቅጣጫ ማስወንጨፏን የደቡብ ኮሪያ ጦር ኤታማዦር ሹም ዛሬ ረቡዕ አስታውቀዋል።

ሚሳዬሎቹ የተተኮሱት በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ሲሆን፣ እንቅስቃሴዎቻቸው በደቡብ ኮሪያና እና በዩናይትድ ስቴትስ መረጃ ድርጅት ክትትል ይደረግባቸው እንደነበር የደቡብ ኮሪያ የጋራ ጦር ኃይሎች አዛዡ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ኮሪያ እና በዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች የሚደረጉ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችና በሰሜን ኮሪያ የጦር መሣሪያዎች ሙከራ መባባሱን ተከትሎ በኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረት ነግሷል።

ፒዮንግያንግ በጦርነት ከተከፈለችው ደቡብ ኮሪያ ጋር እርቅ ለመፍጠር አመላካች የሆነውና በዋና ከተማዋ የሚገኝ አንድ ትልቅ የሰላም ቅስት ባላፈው ቅዳሜ ማፍረሷንም የንግድ ሳተላይት ምስሎች ትንተና አመልክቷል፡፡

ድርጊቱ መሪው ኪም ጆንግ ኡን የሰላማዊ ውህደትን ሀሳብ በማግለል ደቡብ ኮሪያን እንደ ቀዳሚ ባላንጣነት መፈረጃቸውን የሚያመላክት መሆኑን አሶሴይትድ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው ሳምንት ይህ የሰላም ቅስት “ለዐይን በጣም የሚያስጠላ ነው” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ የሰሜን ኮሪያን ህዝብ ከደቡብ ኮሪያ ህዝብ ጋር ለማዋሃድ ለረጅም ዘመን የኖረውን የሰላም ሀሳብ እንዲወገድ ማድረጋቸው ተመልክቷል፡፡

ኪም ጆንግ ኡን ደቡብ ኮሪያን የሰሜን ኮሪያ አደገኛ የውጭ ባላንጣ አድርጎ የሚገልጻት ህገ መንግሥት እንዲጻፍ ትዕዛዝ መስጠታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ዛሬ ረቡዕ የተወነጨፉት የሰሜን ኮሪያ ሚሳዬሎች የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ከገባ ወዲህ ሁለተኛው ክስተት መሆናቸው ተዘግቧል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG