በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኬፕ ቨርድ እና ግብጽ ወደ ቀጣይ ዙር ሲልፉ ፣ ጋና እና ኮትዲዩቫር አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል


.
.

34ኛው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ በኮትዲቯር በቀጠለበት በአሁኑ ሰዓት ያልተጠበቁ ውጤቶች እና ቀልብ ሳቢ ትዕይንቶች የአህጉሪቱን ተወዳጅ ፉክክር ይበልጡኑ አጓጊ አድርገውታል።

ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የኬፕ ቨርድ እና ግብጽ ብሔራዊ ቡድኖች እስከ መጨረሻው ደቂቃ የዘለቀ ፍልሚያ በማድረግ ደጋፊዎቻቸውን በስሜት ቁጭ ብድግ አድርገዋል።

በ46ኛው ደቂቃ በጊለሰን ታቫሬስ አማካይነት ቀድሞ የማግባት ዕድሉን ያገኙት የኬፕ ቨርድ "ሰማያዊ ሻርኮች" መሪነታቸውን ማስጠበቅ የቻሉት ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። የግብጹ ሞሐመድ ትረስጌ በ50ኛው ደቂቃ “ፈርኦኖቹን” አቻ አድርጓል።

የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ዕድሉ ለሚወሰን ያላቀ ሚና በነበረው በዚህ ጨዋታ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ተጫዎቾቹ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ የኬፕ ቨርድን ተከላካዮች አልፈው ግብ ለማስቆጠር ትንቅንቅ አድርገዋል። ግብጾች ጥረታቸው ሰምሮ በ93ኛው ደቂቃ ሙስጠፋ ሞሃመድ በአስቆጠራት ጎል ደጋፊቻቸውን ጮቤ ማስረገጥ ችለው ነበር ። ይሁንና ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰከንዶች ሲቀሩ ፣በ99ኛው ደቂቃ ላይ የኬፕ ቨርድ ብሔራዊ ቡድን በብሬያን ሲልቫ ተዚራ ጁኒየር አማካይነት 2ኛውን ጎል አስቆጥሮ የግብጽ ብሔራዊ ቡድን አባላት እና ደጋፊዎችን ለድንጋጤ ሲዳርግ ፣ የትንሿን ደሴት ደጋፊዎቹን ለዳግም ኩራት አብቅቷል።

በተመሳሳይ ምድብ የተደለደሉት ጋና እና ሞዛምቢክ 2 ለ 2 አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ ግብጽ ከዚህ ቀደም ያስመዘገበቻቸው 3አቻ ውጤቶች ተዳምረው በሁለተኛው ምድብ ከተደለደሉት ሀገራት መካከል ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈች ሁለተኛ ሀገር ለመሆን በቅታለች።

በዘንድሮው ውድድር እጅግ የተቀናጀ ቡድን በማሰለፍ ፣ ሁለት የቀደሙ ጨዋታዎችን ድል አድርጎ ፣ አንድ ጨዋታን በአቻ ለማጠናቀቅ የቻለው የምዕራባዊ አፍሪካ ደሴት የኬፕ ቨርድ ቡድን ከምድቡ በቀዳሚነት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ ተሰናባች መሆኑን ርግጥ ሲሆን ፣ የጋና ጥቁር ክዋክብት በበኩላቸው ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕጣቸው ገና አልተረጋገጠም ። ጋና በምርጥ ሶስተኝነት ከምድቧ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የሌሎች ምድቦች ጨዋታዎች ውጤት መጠባበቅ ግድ ሆኖባታል ሆኗል ።

ተመሳሳይ አጣብቂኝ ውስጥ የገባችው ሌላኛው ሀገር አዘጋጇ ኮትዲዩቫር ናት ። ዛሬ ቀደም ብሎ በተከናወነ ጨዋታ በኢኮቶሪያል ጊኒ 4 ለ 0 የተሸነፈችው ኮትዲዮቫር ለቀጣይ ዙር ካለፉ 16 ሀገራት ለመመደብ የቀሪ ጨዋታዎችን ውጤት ትጠባበቃለች። ኮትዲዩቫር ከተደለደለችበት ምድብ “ኤ” ኢኮቶሪያል ጊኒ እና ናይጄሪያ ወደ ቀጣር ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ ጊኒ ቢሳዎ ከውድድሩ ውጭ ሆናለች ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG