በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጋዛ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ25 ሺህ ማለፉን የጤና ሚኒስትሩ አስታወቀ


እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ25ሺህ አልፏል
እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ25ሺህ አልፏል

እስራኤል ከሦስት ወራት በላይ ባካሄደችው ጦርነት የተገደሉት ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ25 ሺህ በላይ ማለፉን፣ በጋዛ የሚገኘው የጤና ሚኒስትር እሁድ እለት አስታወቀ።


ሚኒስትሩ እንዳለው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በሚካሄደው ጦርነት እስካሁን 25 ሺህ 102 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 62 ሺህ 681 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ብቻ 178 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እና 293 ሰዎች መቁሰላቸውንም አመልክቷል።

ከስካይ ኒውስ ጋር እሁድ እለት ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስትር ግራንት ሻፕስ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የፍልስጤም መንግስት እንዳይመሰረት ተቃውሞ ማሰማታቸው 'አሳዛኝ' ነው ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው፣ አርብ እለት የአስተዳደራቸውን አቋም ሲያስረዱ "ሁለት መንግስታት የመመስረቱ መፍትሄ ሊፈፀም የሚችልበት የተለያየ መንገድ አለ" ያሉ ሲሆን፣ የኔታንያሁ መንግስት ግን ይህን አይቀበልም ሲሉ ተናግረዋል።

ነፃ የሆነ የፍልስጤም መንግስት መመስረት በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ ባይደን አርብ እለት ከኔታንያሁ ጋር የስልክ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ባወጣው መግለጫ፣ ኔታንያሁ "ሐማስ ከተደመሰሰ፣ ጋዛ ከዚህ በኃላ ለእስራኤል ስጋት እንደማትሆን ለማረጋገጥ፣ እስራኤል በጋዛ የፀጥታ ቁጥጥር ሊኖራት እንደሚገባ ያላቸውን ፖሊሲ በድጋሚ አረጋግጠዋል፣ ይህ ደግሞ የፍልስጤምን ሉዓላዊነት ለማረጋጥ የሚደረገውን ጥያቄ የሚፃረር ነው" ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አራተኛ ወሩን ያስቆጠረው ጦርነት በየት አቅጣጫ ይሂድ የሚለው ልዩነት በእስራኤል ካቢኔ ውስጥ እየጨመረ ሲሆን፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በሀገራቸው ውስጥ የሚደረግባቸው ግፊቶችም እያየሉ ነው።

የእስራኤል መሪ በሐማስ ላይ “ሙሉ ድልን” ለመጎናፀፍ እንደሚገፋ በተደጋጋሚ ቢናገሩም፣ ድሉን እንዴት እንደሚያገኙት ግን የተገለጸ ነገር የለም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG