በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የ"ቴራንጋ አናብስት" እና ትንሿ ደሴት  በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ  ገናናነታቸውን ቀጥለዋል 


የ"ቴራንጋ አናብስት" ተብሎ የሚጠራው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ፣ የእግር ኳስ ዘርፍ ኃያልነቱን በማስጠበቅ የካሜሮን አቻውን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ድል አድርጓል ።
የ"ቴራንጋ አናብስት" ተብሎ የሚጠራው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ፣ የእግር ኳስ ዘርፍ ኃያልነቱን በማስጠበቅ የካሜሮን አቻውን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ድል አድርጓል ።

የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (አፍኮን 2023) በምዕራባዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ኮትዲዮቫር ቀጥሏል ። የ"ቴራንጋ አናብስት" ተብሎ የሚጠራው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ፣ የእግር ኳስ ዘርፍ ኃያልነቱን በማስጠበቅ የካሜሮን አቻውን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ድል አድርጓል ። በቻርለስ ኮናን ባኒ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፣ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ከሴኔጋል ቡድን በመጠኑ ሻል ብሎ የነበረው የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን በርካታ የጎል አጋጣሚዎችን ወደ ውጤት መቀየር ባለመቻሉ የሚያስቆጭ ተሸናፊ ሆኗል ። በአንጻሩ አልዩ ሲሴ የሚሰለጥኑት የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን ጥንቃቄ የተሞላበት አጫዋወቱን በጎል በማጀብ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያለውን ዕድል ከፍ አድርጓል። ኢስማኤላ ሳር ፣ ሀቢብ ዲያሎ እና የቡድኑ ፊታውራሪ ሳዲዮ ማኔ ለሴኔጋል ጎሎችን አስቆጥረዋል ። ለካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ብቸኛውን ጎል ያስቆጠረው ጄን ቻርለስ ካስቴሌቶ ነው ።

ዛሬ በተደረገ ሌላ ጨዋታ ከዕለተ ዕለት ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው የትንሿ የምዕራብ አፍሪካ ደሴት ኬፕ ቨርድ ብሔራዊ ቡድን የሞዛምቢክ አቻውን 3 ለ0 በሆነ ውጤት በመርታት ገናናነቱን አሳይቷል ። ቤቤ ፣ ራየን ሜንዴዝ እና ኬቪን ፒና በሞዛምቢክ መረብ ላይ ጎል ያዘነቡት ተጫዎቾች ናቸው። በተለይ ቤቤ በ32ኛው ደቂቃ ከግማሽ ሜዳ ፈንጠር ብሎ ከሚገኝ ስፍራ ከርቀት በመጠለዝ ከመረብ ያገናኛት ጎል በውድድሩ ከታዩ ድንቅ ጎሎች መካከል አንዱ ተደርጎ መጠቀስ ይዟል ። ኬፕ ቨርድ ከዚህ ቀደም የጋናን ብሄራዊ ቡድን 2 ለ1 በሆነ ውጤት መርታቷን ተከትሎ ከወዲሁ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች ። የኬፕ ቨርዴ ቡድን እጅግ ማራኪ ጨዋታ እና የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ቅንጅት ሰኞ ዕለት ብሄራዊ ቡድኑ ከሌላው ጠንካራ የአህጉረ አፍሪካ ቡድን ፥ ግብጽ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በእጅጉ አጓጓጊ አድርጎታል ።

ከአፍሪካ ጠንካራ ቡድኖች መካከል የሚመደቡት የግብጽ እና የጋና ብሔራዊ ቡድኖች በትናንትናው ዕለት የጋለ ፉክክር ማድረጋቸው ይታወሳል ። ጋና ጨዋታውን ለማሸነፍ የሚያበቃትን የቀደመ ዕድል ከእረፍት በፊት በ47ኛው ደቂቃ በሞሃመድ ኩድስ አማካኝነት አግኝታለች ። ይሁንና ከእረፍት መልስ የጋና ተጫዎቾች የፈጸሙትን ስህተት በመጠቀም ኦማር ማርሞሽ በ69ኛው ደቂቃ ግብጽን አቻ የሚያደርጋት ጎል አስቆጥሯል። ጋና ከ2 ደቂቃ በኃላ ቀዳሚውን ጎል ባስቆጠረው ሞሃመድ ኩድስ አማካይነት ሁለተኛውን ጎል አስቆጥራ መሪነቱን መያዝ ችላለች። ሆኖም በ74ኛው ደቂቃ የገና ተጫዎቾች በራሳቸው የጎል ክልል የሚያደርጉትን ያልተናበበ ቅብብል የጠለፈው የግብጹ ሙስጠፋ ሞሃመድ ኳሷን ከመረብ በማገናኘት ሀገሩን ለአቻ ውጤት አብቅቷታል። በዚህ ውድድር ላይ ተሰልፎ የነበረው፣ ለሊቨርፑሉ የቀኝ መስመር ተጫዎች ፣ ከአፍሪካ ምርጥ ተጫዎቾች መካከል አንዱ ስለመሆኑ የሚነገርለት የግብጹ ሞሀመድ ሳላሕ ቋንጃው ላይ የደረሰበትን ጉዳት ተከትሎ በመጀመሪያው የጨዋታው ምዕራፍ በሌላ ተጫዎች ለመቀየር ተገዷል። ግብጽ ከኬፕ ቨርድ ጋር ሰኞ ላለባት ግጥሚያ መጫወት ይችል እንደሁ በዛሬው ዕለት የሕክምና ምርመራ እንደሚደረግለት የብሄራዊ ቡድኑ ሐኪም መናገራቸውን አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG