በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ እና እንግሊዝ በሁቲዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ አምስት ተዋጊዎች መገደላቸው ተገለጸ


ከዩኬ የመከላከያ ሚኒስቴር የተገኘ ምስል እአአ ጥር 11/2024
ከዩኬ የመከላከያ ሚኒስቴር የተገኘ ምስል እአአ ጥር 11/2024

ዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝ እና ሌሎች አጋሮች የሁቲ አማፂያን በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ፣ በዓለም አቀፍ መርከቦች ላይ ላደርሷቸው ተከታታይ ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ተከታታይ የአየር ድብደባ አካሂደዋል። ጥቃቱ በኢራን የሚደገፈውን ቡድን በእጅጉ የሚያዳክም መሆኑም ተገልጿል።

የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ዕዝ ሐሙስ እለት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በተከታታይ የተደረጉት የአየር ድብደባዎች በሁቲ ቁጥጥር ስር በሚገኙ የየመን አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ 16 ቦታዎች ላይ መፈፀማቸውን እና፣ የትዕዛዝ እና የቁጥጥር መስመሮችን፣ የሚሳይል ማስወንጨፊያ እና የምርት ስፍራዎችን ጨምሮ ከ60 በላይ ኢላማዎች መመታታቸውን አስታውቋል።

ስለዘመቻው ዝርዝር ሁኔታ ለመናገር ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ባለሥልጣን፣ "በኃይል እና በጥሩ ሁኔታ ጉዳት አድርሰንባቸዋል" ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የሁቲ አማፂ ቡድን ቃል አቀባይ በበኩላቸው፣ በጥቃቱ ቢያንስ አምስት ተዋጊዎች ሲገደሉ ስድስት ሌሎች መቁሰላቸውን ያስታወቁ ሲሆን፣ ጥቃቱ ጉዳት ስላደረሰባቸው ኢላማዎች ግን አልገለፁም።

አሜሪካ እና እንግሊዝ፣ በአውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ኔዘርላንድ እና ባህሬን እርዳታ ጥቃቶቹን ያካሄዱት ተዋጊ ጀቶችን፣ የውሃ ላይ እና ሰርጓጅ መረከቦችን በመጠቀም መሆኑን የመከላከያ ባለስልጣኑ ገልፀዋል። የሁቲ የጦር ሰፈሮችን ለማጥቃት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ100 በላይ በላይ አነጣጥሮ አውዳሚ ከባድ መሳሪያዎችን መተኮሷንም ገልጸዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ሐሙስ እለት ዋይት ኃውስ ባወጣው መግለጫ፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃቶቹ፣ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መልኩ ሁቲዎች በዓለም አቀፍ የባህር መርከብ ላይ ላደረሱት ጥቃት ቀጥተኛ ምላሽ መሆኑን ገልፅዋል። የዲፕሎማሲ ጥረቶች ችላ በመባላቸው አስፈላጊ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በተመሳሳይ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የሁቲ ጥቃቶች አለመረጋጋት መፍጠራቸውን በመግለፅ አውግዘው፣ የእንግሊዝ ተዋጊ ጀቶች በሐሙሱ ጥቃት ላይ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG