በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከአየር ላይ ተገንጥሎ የወደቀው የቦይንግ አውሮፕላን በር ተገኘ


 በፖርትላንድ ኦሪገን ባለፈው ሣምንት በበረራ ላይ ሳለ ተገንጥሎ የወደቀው የአላስካ አየር መንገድ ቦይንግ አውሮፕላን
በፖርትላንድ ኦሪገን ባለፈው ሣምንት በበረራ ላይ ሳለ ተገንጥሎ የወደቀው የአላስካ አየር መንገድ ቦይንግ አውሮፕላን

ባለፈው ሣምንት በበረራ ላይ ሳለ ተገንጥሎ የወደቀው የአላስካ አየር መንገድ ቦይንግ አውሮፕላን በር፣ በፖርትላንድ ኦሪገን አንድ ግቢ ውስጥ መገኘቱን የአሜሪካው ብሔራዊ የመጓጓዣ ደህንነት ቦርድ አስታውቋል።

የአላስካ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን፣ ባለፈው ዓርብ ከፖርትላንድ አየር ማረፊያ ተነስቶ በበረራ ላይ ሳለ፣ በሰዎች መሣፈሪያ አካሉ ላይ የነበረ በር ተገንጥሎ ወድቋል። አብራሪዎች ወዲያውኑ አውሮፕላኑን መልሰው አሳርፈዋል። 177 መንገደኞች እና 6 የበረራ ቡድኑ አባላት ካለምንም ጉዳት ሊያርፉ መቻላቸው ታውቋል።

የደህንነት ቦርዱ በተመሳሳይ መልክ የተሠሩ 171 ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ግዜያዊ እገዳ ጥሏል። የአላስካ አየር መንገድም 170 የሚሆኑ በረራዎቹን ሲሰርዝ፣ 25 ሺሕ የሚሆኑ መንገደኞች ተስተጓጉለዋል።

ተገንጥሎ የወደቀው በር በአንድ መኖሪያ አጥር ግቢ ውስጥ መገኘቱን እና የአደጋውን ምክያት ለማወቅ የሚደረገውን ምርመራ እንደሚረዳ ቦርዱ አስታውቋል።

ክስተቱ ማክስ 7 እና ማክስ 10 ለተሰኙ አውሮፕላኖቹ የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ጥረት የሚያደርገውን የቦይንግ ኩባንያ ተጨማሪ ምርመራ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮአጵያ አየር መንገድ እና በኢንዶኔዢያው ላየን አየር ንብረትነት የሚንቀሳቀሱ ሁለት ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ተከስክሰው 346 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG