በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሂዝቦላህ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኮሰ


የመካከለኛው ምስራቅ ታጣቂ ቡድኖች
የመካከለኛው ምስራቅ ታጣቂ ቡድኖች

የሊባኖስ ሚሊሻ ቡድን ሄዝቦላህ ዛሬ ቅዳሜ ከ60 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ጦር ሠፈር መተኮሱን ገልጿል።

የሚሳዬሉ ጥቃት በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ለተገደሉትና ከመሪዎች አንዱ ለሆኑት ሳሌህ አል አሩሪ የተሰጠ “የመጀመሪያ ምላሽ” ነበር ሲል ሂዝቦላህ በመግለጫው አስታውቋል።

ሂዝቦላህ አሩሪን ለገደለው ጥቃት እስራኤል ተጠያቂ ናት ብሎ ቢያምንም እስራኤል ግን ኃላፊነቱን አልወሰደችም።

የሊባኖስ ታጣቂዎች ቡድን መሪ ለጥቃቱ አፀፋዊ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል ሲሉ ትናንት ዓርብ ተናግረው ነበር ።

"ስለዚህ አሳሳቢ ጥሰት ዝም ማለት አንችልም" ሲሉ የቡድኑ መሪ ሀሰን ናስራላህ መናገራቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ናስራላህ “አጸፋውን ከመመለስ ይልቅ ዝም ማለት የሚያስከፍለው ዋጋ እጅግ የላቀ ነው” ማለታቸውም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

እስራኤል ኃላፊነቱን በቀጥታ ባትቀበልም ሐማስ እና የአከባቢው የጸጥታ ባለስልጣናት ሳሌህ አል አሩሪን የገደለው የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ነው ብለዋል።

ሂዝቦላህ - ልክ እንደ ሃማስ፣ በኢራን የሚደገፍ ታጣቂ ቡድን ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች በአሸባሪነት የተፈረጀው ነው፡፡

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከጀመረበት ጥቅምት ወር አንስቶ ሂዝቦላህ በእስራኤል ሰሜናዊ ድንበር አቅጣጫ ሮኬቶችን እንደሚተኩስ ተዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ዛሬ ቅዳሜ ማለዳው ላይ በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ እና ካን ዩኒስ ከተሞች ላይ ጥቃት አድርሳለች።

የእስራኤል ባለስልጣናት ባዘዙት መሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን አካባቢያቸውን ለቀው ከድብደባው ለማምለጥ ወደ ደቡብ ጋዛ ለመሸሽ ቢሞክሩም ውጊያው እዚያም የተከተላቸው መሆኑ ተመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ሃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ፣ አብዛኛው የጋዛን ክፍል ወደ ፍርስራሽነት የቀየረው እና ትልቅ የሰብአዊ ቀውስ በመፍጠር ለሶስት ወራት የዘለቀውን ጦርነት ተከትሎ፣ መላው የፍልስጤም ግዛት “ለመኖሪያነት የማይመች ሆኗል” ሲሉ ትናንት ዓርብ ዓርብ አስጠንቅቀዋል፡፡

በኢራን የሚደገፈው ሐማስ እ.ኤ.አ ጥቅምት 7 እስራኤል ላይ የሽብር ጥቃት በመክፈት 1,200 የሚጠጉ ሰዎችን ገድሎ 240 የሚጠጉ ሰዎችን ካገተበት ጊዜ አንስቶ፣ መካከለኛው ምስራቅ የግጭት ቀጠና ሆኖ ቆይቷል ስትል እስራኤል ተናግራለች።

ከታጋቾቹ መካከል የተወሰኑት የተለቀቁ ሲሆን 130 ያህሉ አሁንም በጋዛ ይገኛሉ።

የእስራኤል ለዚህ ጥቃት እየሰጠችው ባለው ምላሽ ከ22,600 በላይ ፍልስጤማውያንን ተገድለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG